በመኮንን ተሾመ ቶሌራ (ከአዳማ)
ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ፣ የክረምት ወራት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ አስፈላጊዉን ዝግጅት እንዲያደርግ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
የክረምት ወራት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት ማለትም የሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ምዕራብ፡ ደቡብ ምዕራብ፤ መካከለኛው፤ ሰሜን ምስራት እና ምስራቅ አካባቢች የሚኖሩ ዜጎች በክረምት ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና የሚገኘውን ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት በአግባቡ በመጠቀም በወቅቱ የሚካሄደውን የግብርና እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር እንዲያከናዉኑ ሲል ኢንስቲትዩቱ አስጠንቅቋል፡፡
ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብና ሊወሰዱ የሚገባቸዉ የጥንቃቄ ስራዎች
ዛሬ በአዳማ ከተማ በተካሄደው ሰብሰባ ላይ ያለፈው የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማና በሚቀጥለው የክረምት 2016/17 ዓ.ም ወቅት በሚጠበቀው የወቅት እየር ጠባይ አዝማሚያን አስመልክቶ ገለጻ የተደረገ ሲሆን የክረምቱ ዝናብ አጀማመር በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገራቱ አክባቢዎች ላይ ቀድሞ እንደሚጀምርና በአወጣጥ ረገድ ግን ሊዘገይ እንደሚችል ተገልፆል፡፡
ይህን አሰመልክተዉ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያስከትሉ ከሚችሉ ምክንያቶች አንዱ በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከመደበኛ በታች መሞቅ (ENSO-LA NINA) ሲሆን እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀትም ከመደበኛ በላይ (Positive IOD) ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ስለሚያሳዩ ነዉ ብለዋል!
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የደቡብ የሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ከሚጠበቀዉ Positive IOD ክስተት ጋር በተያያዘ በነሀሴና በመስከረም ወራቶች ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም በአብዛኛዉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከመደበኛዉ እንፃራዊ መጨመር እንደሚኖረዉም አንስተዋል።
አቶ ፈጠነ አክለዉም አልፎ አልፎ ከሚኖረዉ ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ጋር በተያያዘ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑት ረባዳማ ቦታዎች፤ የወንዝ ዳርቻዎች እና በከተሞች አካባቢ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሥራዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እንዲያስችል አስፈላጊዉን የጥንቃቄ ስራ ከወዲሁ በቅንጅት መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ያለፈው የበልግ ወቅት ተመሳሳይ ትንበያና ዉጤቱ
ኢንስቲትዩቱ በወቅቱ በሰጠዉ መግለጫም ባለፈው የበልግ ወቅት በተሰጠዉ ትንበያ መሠረት በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛዉ በላይ በሆነ የአየር ጠባይ ተፅዕኖ ስር እንደቆዩ ተብራርቷል፡፡
“ከዚህም ሌላ በበልግ ወቅት በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ ምስራቅና መካከለኛዉ ክፍሎች ከመደበኛው በላይ መሞቅ (ENSO-EL NINO) እንዲሁም የሰሜን ህንድ ውቅያኖስ ከመደበኛው በላይ መሞቅ (Positive IOD) ተጽዕኖ ሥር በመቆየቱ ለወቅቱ ዝናብ ከመደበኛ በላይ መሆን ዋነኛ መንስኤ ነበር፡፡” ሲል መግለጫዉ ጠቁሟል።
እንደ መግለጫዉ ከሆነ በአጠቃላይ ባለፈው የበልግ ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደተስተዋለባቸውና ይህም ሁኔታ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ለሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ እንደነበር ተብራርቷል፡፡
በተጨማሪም የነበረው ዝናብ በእነዚህ አከባቢዎች ለግብርና ሥራ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለመጠጥ ውሃ እና ለግጦሽ አቅርቦት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደረገ እንደነበር ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ በሰሜን አጋማሽ፣ በመካከለኛው እና በምስራቅ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ የነበረው ቅጽበታዊ ጎርፍ ያስከተለ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ የነበረ ሲሆን ይህም ሁኔታ በግብርና፣ በሰው ህይወት እና በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳደረሰ የተሰበሰቡ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ኢንስቲትዩቱ አሰረግቷል፡፡