በ መኮንን ተሾመ ቶሌራ
በሀገራችን ኢትዮዽያ እና በሌሎች የኤዥና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት በስፋት የሚገኘዉ ስፓሩሊና አልጌ እጅግ በጣም በፕሮቲን የበለፀገና ተፈጥሮአዊ ምግቦችን፣ ተፈጥሮአዊ ነዳጅን እንዲሁም ተፈጥሮአዊ ፕላስቲኮችን ለማምረትና ለማቀነባበር የሚያገለግል ድንቅ ባለአንድ ህዋስ (Unicellular) ተክል ነዉ።
በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮዽያ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች አካባቢ በአብዛኛዉ የፍላሚንጎ ወፎች ምግብ ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል።
ኩሬዎች፣ ሀይቆች እና ወንዞችን ጨምሮ በብዙ ንጹህ የውሃ አካላት ላይ ተንሳፎ ይበቅላል። ሰማያዊ-አረንጓዴ ቀለም ያለዉ ደቂቀ ተክል ከአንዳንድ ተባዮች ፣ ንክኪዎችና የተክል በሽታዎች ነፃ ተደርጎ ብዙ የፀሐይ ብርሃን እና መጠነኛ የሙቀት መጠን ባለበት የዉሀ አካል ላይ በብዛት ሊስፋፋ ይችላል።
ስፓሩሊና አልጌ “ከምግቦች ሁሉ የላቀ ታላቅ ምግብ“
በሰማያዊ-አረንጓዴ ቀለሙ የሚታወቀዉ ደቂቅ ተክል ስፓሩሊና አልጌ (Arthrospira) በፕሮቲን እና በአስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ በመሆኑ በምግብ የተጎዱ ሰዎችን በተለይም ህፃናትን በከፍተኛ ሁኔታ ይታደጋል ተብሎ ታምኖበታል።
በጥራት መመረት ከቻለም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እጅግ በጣም ተፈላጊ በመሆኑ በእያንዳንዷ ግራም ጠቀም ያለ ዶላር የሚታፈስበት በመሆኑ ስፓሩሊና አልጌን በስፋት ለማምረት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ስፓሩሊና አልጌ ስሙን ያገኘዉ በማይክሮ ስኮፕ ሲታይ ቁልጭ ብሎ ከሚታየዉ እንደ ስፕሪንግ ሽቦ የተጠቀለለና ክብ ከሆነዉ ቅርጹ ነው።ደቂቀ አልጌዉ የፀሐይ ብርሃንን ወደ ሀይልነት የመለወጥ አስደናቂ ብቃትም ያለዉ ነዉ።
ደቂቀ አልጌዉ በተፈጥሮ በጨዋማ ሀይቆች ላይ በስፋት ተንሳፎ የሚበቅል ሲሆን በዉስጡ ከያዛቸዉ ንጥረ ነገሮች መካከል ከ60% በላይ የሚሆነዉ ጠቃሚ ፕሮቲን ነዉ። ይህም ለትክክለኛ እድገት እና የማሰብ ችሎታ መጨመር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ፕሮቲን በሰውነታችን ውስጥ በእያንዳንዱ ነጠላ ሕዋስ ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል እና ጡንቻዎቻችንንም ለመገንባት እና የጡንቻን የኃይል መጠን ለመጨመር ወሳኝ ነዉ።
ስፓሩሊና አልጌ ካለዉ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን በተጨማሪ ሊሎች ንጥረ-ነገሮችን በመያዝ በአለም ላይ ሌላ ምንም አይነት ምግብ አይወዳደረዉም።
በዉስጡ ከያዛቸዉ ንጥረ-ነገሮችን መካከል ቫይታሚን ኤ (ቤታ ካሮቲን) – ለአጥንት እድገትና ለጥሩ እይታ ፣ ቫይታሚን B2 (Riboflavin) – ለጤናማ የደም ሴሎች እና የኃይል መጠን መጨመር ፣ ቫይታሚን B9 (ፎሊክ አሲድ) – ጡንቻዎችን ለመገንባት እና የሕዋስ እድገትን እንዲሁም የሂሞግሎቢንን ምርትን ለመጨመር ፣ ቫይታሚን B12 – በሰውነት ውስጥ ካርቦሃይድሬትን ወደ ግሉኮስ ለመለወጥ እንዲሁም ሃይልን ለማምረትና የሰውነትን ድካምን ለመቀነስ ፣ ቫይታሚን ሲ (አስኮርቢክ አሲድ) – አጥንትን ፣ የደም ሥሮችን ወዘተ ጨምሮ የግንኙነት ሕብረ ሕዋሳት እንዲፈጠሩ እና እንዲቆዩ ለመርዳት የሚያስፈልጉ ቫይታሚኖችን በዉስጡ አምቆ ይዟል።
በተጨማሪም የአስፈላጊ ኃይል ሰጪ ማዕድናትም ምንጭ ነዉ። ለምሳሌ ዚንክ ለስነ-ተዋልዶ ብቃት መጨመር፣ ለጡንቻዎች እድገት እና ጥገና ይረዳል ።ማንጋኒዝ በበኩሉ በሰውነት ውስጥ ሜታቦሊዝምን በማስተካካል ትልቅ ሚና ይጫወታል፣ ድካምን ይቀንሳል ፣ የጡንቻ ስንጥቆች እና እብጠት ይጠግናል። ፎስፈረስ ደግሞ የጡንቻ እና ጾታዊ ድክመትን ያስተካክላል። ከነዚህ በተጨማሪ ስፓሩሊና አልጌ ከፍተኛ የብረት፣ ካልሲየም እና የፖታስየም – ንጥረ ነገሮች መገኛ ነዉ።
ከጎንዮሽ ጉዳቶች ነፃ የሆነ ብቸኛ መድሃኒት
በመሆኑም በአለማችል በአሁኑ ጊዜ ስፓሩሊና አልጌ ለተጨማሪ ምግብነትና ለመደሀኒትነት ለሚዉሉ ክኒኖችና እንክብሎችን ለማምረት በግበአትነት በብዛት ይፈለጋል። ስፓሩሊና በመግብነትና በመደሀኒትነት ሲዉል ምንም የሚታወቁ የጎንዮሽ ጉዳቶች ወይም አሉታዊ ግብረመልሶች አልተመዘገቡበትም።
የህፃናትን ቅንጨራነት ለመታደግ ፍቱን መፍትሄ
ቅንጨራ (Stunting) የልጆች በፕሮቲን እጥረት መጠቃት ሲሆን የአካልና የአይምሮ እድገትን የሚገታ ችግር ነዉ። ሌላዉ ችግሩ አንድ ሰዉ በቅንጨራ ከተጠቃ የአካልና የአይምሮአዊ እደገቱ በጣም የተጎዳ ሆኖ ሊሻሻል የሚችልበት እድል የለዉም። ችግሩ ያጋጠመው ሰው በአካል ምርታማ መሆን የማይችል ከመሆኑም በላይ አይምሮውም ስለሚጎዳ ትምህርትን ለመቀበልም አይችልም። ወደ ልጅም የመተላለፍ እድል ስላለዉ በጣም አሰከፊ የጤና ችግር ነዉ።
በተጨማሪም በቅንጨራ የተጎዳ ሰዉ ለተደጋጋሚ ኢንፌክሽን እና የስነ-ልቦና ችግሮች ያጋጥመዋል። በኢትዮጵያ በህፃናት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ አገራዊ ችግር ነዉ፡፡ በእርግዝናና ፅንስ እድገት ጊዜ እና ከአምስት ዓመት በታች በሆነ የሕፃናት እድሜ ላይ በሚከሰት የሥርዓተ ምግብ መዛባት የሚመጣ የጤና ችግር ነዉ። እ.ኤ.አ. በ2,000 ከነበረበት 58 በመቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 37 በመቶ ቢወርድም አሁንም ብዙ መሰራት ይኖርበታል፡፡
በሀገራችን የቅንጨራ ምጣኔ እ∙አ∙አ በ2000 47.9%፣ በ2005 43.3%፣ በ2011 37.3%፣ በ2016 36.6%፣ እና በ2019 35.9%፣ በ2019 35.9%፣ በ2000 47.9% የነበረ ሲሆን በብዛት በሰሜናዊ (ትግራይ)፣ በሰሜን ማእከላዊ (አማራ) እና በሰሜን ምዕራብ (አማራ) የኢትዮጵያ ክፍሎች በከፍተኛ ሁኔታ ይታያል።
በሀገሪቱ ለጤና ጠቃሚ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን የሚመገቡ ከስድስት እስከ 23 ወራት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናት ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮዽያ ተጠሪነቱ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነና የአገሪቱን የምግብና ሥርዓተ ምግብ ሥራዎች ትግበራን የሚያስተባብር፣ የብሔራዊ የምግብ ሥርዓትና የሥርዓተ ምግብ ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወቃል፡፡
የመጀመሪያዉ የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርምርና ማምረቻ ማዕከል
በመሆኑም በሀገራችን ያለዉን የስነ-ምግብ በተለይም የፕሮቲን እጥረትን ለመቅረፍና ለሀገሪቱ ተጨማሪ የዉጬ ምንዛሪ ለማስገኘት በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርምርና ማምረቻ ስፍራ ሰሞኑን በአዳሚ ቱሉ የግብርና ምርምር ማዕከል ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል።
የዚህ ደቂቅ ህዋስ መመረት በመቀንጨር ችግር እየተጠቁ ለሚገኙ ከሰሀራ በታች ላሉ ሀገራት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ይታመንበታል። እናም አዲስ የተመረቀዉ የአዳሚ ቱሉ የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርምርና ማምረቻ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠቱ በላይ ኢትዮጵያ በኪሎ 20 ሺሕ ብር በኩንታል ደግሞ እስከ 2 ሚሊየን ብር ገቢ የሚያስገኝ አልጌ በስፋት እንድታመርት የሚያግዝ ነዉ፡፡
በባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካኝነት እዉን የሆነዉ የምርምርና ማምረቻ ስፍራ 1 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የግንባታ ወጪ የተደረገበት ነዉ። በወር ከ30 ኪሎ ግራም በላይ ማይክሮ አልጌ ማምረት እንደሚያስችል በምረቃ ሰነ-ስርዓቱ ላይ ተነግሯል።
በምረቃ ሰነ-ስርዓቱ ላየ የተገኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ መንግስት ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ በመቅረጽ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው ይህ ስራ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ በራሳችን ሃብት፣ የምርምር አቅም እና የሰው ሃይል መልማት እንደምንችል ያረጋገጠ ስራ ነው ብለዋል።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ ደግሞ በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮች በማከናወን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የስፓይሮሊና ሃብት የሕጻናት የመቀንጨር ችግርን ለመቀነስ ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል ።
የስፖይሮሊና ምርምርና ማምረቻ እንደሀገር የሥነ ምግብ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የተገኘውን ውጤት የበለጠ ከፍ ለማድረግ አጋዥ እንደሚሆንም ተጠቅሷል ።
በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማይክሮ አልጌ መሪ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሀብቴ ጀቤሳ በበኩላቸዉ እንደገለጹት ስፓሩሊና ከ90 በመቶ በላይ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን የምግብ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ሲሆን በአለም ላይ አምስቱንም አስፈላጊ ንጥረነገሮች በነጠላ ህዋስ (single cell) የያዘ ብቸኛው ማይክሮ አልጌ ነው፡፡
ሌላው ስፖሮሊናን ለየት የሚያደርገው እንደሌሎች ምርቶች አመትና ወራትን እየጠበቀ ሳይሆን ምርት የሚሰጠው አንዴ መመረት ከጀመረ በየ24 ሰዓቱ ምርት ይሰጣል ብለዋል፡፡
መንግስት ባለሀብቶችን ለመደገፍ ተዘጋጅቷል
ከአራት አመታት በፊት በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቅጥረ ግቢ በላቦራቶሪ ደረጃ እና በቅርቡ ደግሞ በአዳሚ ቱሉ የግብርና ምርምር ማዕከል ደግሞ ከፍ ባለ የማምረቻ ስፍራ ሲካሄድ የነበረው የማይክሮ አልጌ ምርምርና የናውና ምርት የተሳካና አመርቂ ውጤት የተገኘበት መሆኑ የመንግስት ሀላፊዎቹ ይፋ አድርገዋል። ዘርፉ ሊያድግ የሚችለዉም የግል ባለሀብቶች በዘፉ በስፋት ሲሰማሩ መሆንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ከዚህ በኋላ በጣም አትራፊ የሆነውን የስፖሩሊና ማይክሮ አልጌን ለማምረት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችን መንግስት ጥሪ ያቀርባል ያሉት ሀላፊዎቹ በትርፋማው ዘርፍ ለሚሰማሩም ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ትብብርም ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ ስፓሩሊና አልጌ ምን ወስነዋል ?
እ.ኤ.አ. በ 1974 የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ኮንፈረንስ ስፓሩሊናን “የወደፊቱ ምርጥ ምግብ” ብሎ አውጇል።
የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አባል ሀገራት ፣ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የግሉ ሴክተር ስፓሮሊናን ምርትን እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርቧል።
የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) እንዳስታወቀው ደግሞ “ሁለቱም ብሄራዊ መንግስታትም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስፓሩሊናን በመጠቀም የምግብ ዋስትና ፍላጎቶች ለማሟላት ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ምክረ-ሀሳብ አቅርቧል። በተጨማሪም ድርጅቱ “የአካባቢ በድህነትን በጠበቀ መልኩ ለ ስፓሩሊና ምርት ቴክኒካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መፍትሄዎችን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።
የዓለም የጤና ድርጅትም (WHO) በበኩሉ እንዳወጀው ስፓሩሊና በብዙ ምክንያቶች አስፈላጊ ምግብ ነዉ ፣ በብረት እና በፕሮቲን የበለፀገ እና ለህፃናት ያለ ምንም ስጋት ሊሰጥ የሚችል ነዉ።