በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕገወጥ ሰፈራዎችን እና ግንባታቸውን መጀመራቸው ተገለጸ።
ግድቡ ሙሉ በሙሉ ከመጠናቀቁ በፊት ከወዲሁ የተለያዩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በዙሪያው በሕገወጥ መንገድ ይዞታዎችን በመያዝ ሆቴሎችን መገንባት፣ ዓሳ ማስገር፣ የጀልባ አገልግሎት መስጠት እንዲሁም በሐይቁ ዙሪያ ሕገወጥ ሰፈራዎች መስፋፋት መጀመራቸውን ታውቋል ሲል መረጃ ዜና ጠቁሟል
ይህን ያለው የቦሮ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ እንደዚህ ዓይነት ግልጽነት የጎደላቸው ሕገወጥ አካሄዶች ነገ ሌላ ስጋት እንዳይሆኑ በጥንቃቄ መመራት አለባቸው ሲል አሳስቧል።
ስለሆነም ከግድቡ ዙሪያ ተያያዥ በሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች አወሳሰንና አፈጻጸም በተመለከተ የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ግልጽ አሰራርና ፖሊሲ ኖሯቸው በግልጽነት እንዲሠሩ ፓርቲው ጠይቋል ሲል አዲስ ማለዳን ዋቢ ያደረገዉ መረጃ ዜና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገኛ እንደመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ከፕሮጀክቱ ትሩፋቶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባው ገልጿል ። የክልሉ ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ግልፅ አሰራርና የፖሊሲ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ ይገባል ብሏል።
በሌላ በኩል ፓርቲው፤ ‹‹የክልሉ ሕዝብ በነበረው የሰላም እጦት የተነሳ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የመሳተፍና የሚፈልገውን መርጦ በመረጠው መንግሥት የመተዳደር እድል አላገኘም።›› ብሏል። አሁን ላይ በክልሉ የተሻለ የሰላም ሁኔታ በመኖሩ የተያዘው ዓመት ከመገባደዱ በፊት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በክልሉ ምርጫ እንዲያካሂድ ጥሪ አቅርቧል።
በክልሉ በ71 የክልል ምክር ቤት እና በስድስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ አለመካሄዱንም ጠቅሶ፤ በዚህም ምክንያት በሕዝብ የተመረጠ ክልላዊ መንግሥት አልተደራጀም ብሏል።
ፓርቲው እንዲሁም የክልሉን ልዩ ኃይል የማደራጀት ውሳኔ ላይ ሐሳብ ሰጥቷል። በዚህም ‹‹የክልላችን ልዩ ኃይል የተቋቋመው በክልሉ ካብኔ በጸደቀ ደንብ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት በቅድሚያ የማቋቋሚያ ደንቡን ሕጋዊ አካሄድን ተከትሎ መሻር ይኖርበታል። በአፈጻጸሙ ላይም በክልሎች መካከል የመርሃ ግብር ልዩነት ሊኖር አይገባም›› ሲል ገልጿል።