By African Demystifier
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ራሳቸውን ‘ነብይ፣ ፓስተር’ እያሉ በሚጠሩ ሰዎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየታዩ ነው።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ እነዚህ በተከታዮቻቸው ‘ፓስተር’፣ ‘መጋቢ’፣ ‘ነብይ’፣ ‘የእግዚአብሔር ሰው’ ተብለው በሚጠሩ ሰዎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገርያ ከሆኑ ቆይተዋል።
ጉዳዩ በወንጌል አማኞች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከእምነቱ ውጪ ያሉ ሰዎችም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትችታቸውን እንዲሰነዝሩ፣ ምን እየሆነ ነው? በማለት አንዲጠይቁ አድርጓል።
እነዚህ ሰዎች ገንዘብን እንደሚያበዙ፣ በመንፈሳዊ ኃይል ገንዘብ ወደ ባንክ ሒሳብ እንደሚያስገቡ፣ ከአምላካቸው ጋር ሲደባደቡ እንደሚያድሩ፣ የተለያዩ ፈውስ እና ተዓምራቶችን እንደሚያደርጉ ሲናገሩ በይፋ ተደምጠዋል።
ከፍ ሲል ደግሞ ሙታንን አስነሳለሁ በማለት መቃብር ያስቆፈረ እንዲሁም ሴቶችን ደፍሮ የተፈረደበት እንዳለም ተዘግቧል።
ቢቢሲም ያነጋገራቸው የእምነቱን ተከታዮች እነዚህን ክስተቶች መታዘባቸውን በአንድ ድምጽ ‘ምን ጥርጥር አለው። የአደባባይ ምስጢር ነው’ ካሉ በኋላ፣ ክስተቱ በቅርብ በሚያውቋቸው እና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ላይ ሲደርስ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መመልከታቸውን አረጋግጠዋል።
በለንደን በሚገኝ ቤተክርስቲያን መጋቢ የሆኑት ጳውሎስ ፈቃዱ “እነዚህ ወንጌላዊ ክርስቲያኖችን አይወክሉም፤ ከእኛም ጋር በሃይማኖት አንድ አይደሉም። እነርሱ ነን ስላሉ ብቻ የእኛ አካል አድርገን አንወስዳቸውም። በሃይማኖት አንድ አይደለንም፤ እኛንም ሊወክሉን አይችሉም” ሲሉ ጠንከር ያለ ትችታቸውን ይሰነዝራሉ።
የወንጌላዊ አብያተ ክርስትያናት ኅብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት መጋቢ ጻድቁ አብዶም፣ በመጋቢ ጳውሎስ ሀሳብ ይስማማሉ።
የሥነ መለኮት መምህሩ ተካልኝ ነጋ (ዶ/ር ) በበኩላቸው በምዕራቡ ዓለም እነዚህ ሰዎች የሚጠሩበት ስያሜ ፓስቶፕረነር (pastopreneur ) እንደሚባል በመጥቀስ “ነጋዴዎች” ይሏቸዋል።
ፓስቶፕረነር የሚለው ቃል የተገኘው ኢንተርፕነር ከሚለው ቃል ‘ፕረነር’፣ ፓስተር ከሚለው ፓስቶ ተወስዶ መሆኑ ነው።
እነዚህ በነጋዴነት መንፈስ መንፈሳዊ ተቋማትን የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች፣ ከገንዘብ ባሻገር ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው ጨካኝ ወንበዴዎች ተብለው እንደሚፈረጁም ያብራራሉ።
ሐሰተኛ ነብያት ለምን ተበራከቱ?
እነዚህ ሐሰተኛ ነብያት ‘የፈሉት’ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንዳልሆነ መጋቢ ጻድቁ አብዶ እና መጋቢ ጳውሎስ ፈቃደ ይጠቅሳሉ።
በእርግጥም እንዲህ አይነቱ ልምምድ በናይጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በዛምቢያ እንዲሁም በአንዳንድ የሰለጠኑ አገራት ውስጥም የሚታይ እና ወጣ ያሉ ድርጊቶቻቸውም በመገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ ቆይቷል።
መጋቢዎቹ ይህ አይነቱ የስህተት ትምህርት እና ልምምድ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተለይ ይላሉ መጋቢ ጻድቁ፣ “ቡሽሪ የሚባል ግለሰብ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህንን መንገድ ለመከተል ሞክረዋል።”
ቢቢሲ ባነጋገራቸው ወንጌላውያን አማኞች ምልከታ ለገዛ ምኞታቸው ቅዱሳት መጻህፍትን እያጣመሙ ኪሶቻቸውን ማደለብ የሚፈልጉ ሰዎች ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ እጅጉን በርክተዋል።
ከዚህ ባሻገር በርካታ እምነቱ ተከታዮች የሚስማሙበት ለእነዚህ ሐሰተኛ ነብያት መበራከት አንዱ ምክንያት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በማዕከል የሚገዛ የክርስትና ትውፊት አለመሆኑ ነው።
በዚህም የተነሳ ግለሰቦች ጭምር የራሳቸውን አብያተ ክርስቲያናት መክፈት የሚችሉበት ዕድል አላቸው ይላሉ።
ይህ ዕድል ከዚህ በፊት በቤተክርሰቲያናት ውስጥ ሰዎች እየተፈተሹ፣ ብቃታቸው እና ‘ጤናማነታቸው’ እየተረጋገጠ ወደ እንደዚህ አይነት አገልግሎት ውስጥ የሚገቡበትን ሥርዓት በመቋረጡ ያለ አንዳች ተጠያቂነት የራሳቸውን መድረክ ፈጥረው እንደፈለጉ የሚሆኑበት ዕድል ተፈጥሯል ይላሉ የሥነ መለኮት መምህሩ ተካልኝ (ዶ/ር)።
“የኢህአዴግን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በቂ ዝግጅት እና ሥልጠና ሳይኖራቸው በአዳዲስ አማኞች መጥለቅለቃቸው፣ እንዲሁም የአመራርነት ቦታዎቹ በእነዚህ ሰዎች በፍጥነት መያዙ የጎዳን ይመስለናል” የሚሉት ደግሞ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሥነ መለኮት መምህር ናቸው።
ቤተ ክርስቲያኒቷ የእምነት ነጻነትን ስታገኝ በሮቿን ወለል አድርጋ በመክፈቷ በተለይ ከኢትዮጵያ ውጪ የተለያዩ አስተምህሮዎችን ይዘው ለመጡ ግለሰቦች ራሷን ያለበቂ ዝግጅት አጋልጣ ሰጥታለችም ይላሉ።
“የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች አጥለቀለቁን” የሚሉት እኚህ ምሁር፣ መንፈሳዊ ጥንካሬ እየተሸረሸረ ኅብረትን በመፈለግ ብቻ ከቦታ ወደ ቦታ መባዘን በማኅበረ ምዕመናን ዘንድ መስተዋሉን ያነሳሉ።
ጴንጤቆስጣል ሲስፋፋ ‘ምርቱን ከግርድ’ ሳይለዩ ሁሉም ቤተ እምነቶች እንቅስቃሴውን ተቀብለዋል በማለት፤ ይህም አዲሱን ትውልድ የሚዋጅ አገልግሎት በቤተ እምነቶች ዘንድ እንዳይገኝ ማድረጉን እና በግለሰቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የሥነ መለኮት መምህሩ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጴንጤቆስጣዊ እና የካሪዝማቲክ ትውፊትን የሚከተሉ የወንጌል አማኞች ማኅበረሰብ፣ ካላቸው ወደ ፊት የሚሆነውን ከመጠበቅ ጋር ነው የሚያያዘው ይላሉ።
እነዚህ የካሪዝማቲክ እና ጴንጤቆስጣዊ የእምነት እንቅስቃሴ ትውፊትን የሚከተሉ አማንያን
“እግዚአብሔር መግቦታዊ አገዛዙ በመካከላችን ከሚሰራበት መንገዶች መካከል አንዱ የፀጋ ስጦታን በእኛ መካከል ማፍሰሱ ነው” ብለው ያምናሉ።
በተለይ ደግሞ የክርስቶስ ዳግም መምጣት እየቀረበ በመጣ ቁጥር ይህ የጸጋ ስጦታ አገልግሎት እየበዛ ይመጣል የሚል ጥበቃ እንዳላቸው ያብራራሉ።
ይህ ጥበቃን ሐሰተኛ ነብያት እና ፓስተሮች፣ ጥበቃው ላይ እንዲነግዱበት እና አገልግሎቱን የሚቀበሉትን ሰዎች ደግሞ በልበ ሰፊነት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አድርጓል ሲሉ ያክላሉ።
የሥነ መለኮት ምሑራኑ በንጽጽሮሽ የወንጌላውያን አማኙ ማኅበረሰብ፣ በተለይ በደርግ ጊዜ ይህ ነው የሚባል ሀብት ማከማቸት የሚችል አልነበረም። በእምነቱ በጣም የሚሰደድ የነበረ ነው። በዚህም የተነሳ የወንጌላውያን ክርስትና ትውፊትን መከተል በሆነ መልኩ ራስን ለስደት ማዘጋጀት እንደነበር ያነሳሉ።
“በአገልግሎት ውስጥ ወደ ማንም ኪስ የሚተርፍ አልነበረም። በመስዋዕትነት ጭምር የሚደረግ የአገልግሎት ዓይነት ነው። አሁን ግን ቤተክርስቲያን ከዚህ ስደቷ ስትገታ ልክ በሌላ የእምነት ዘርፎች ውስጥ እንዳሉ ሰዎች ሁሉ ሰዎች ገንዘብ ማካበት ሲጀምሩ ይህንን ገንዘብ ጤናማ ባልሆነ መልኩ ወደ ኪሱ ማስገባት የሚፈልግ ሰው መፈጠሩ አይቀርም” ይላሉ ተካልኝ (ዶ/ር)።
መጋቢት 22/2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ ባወጣው መግለጫ ላይ በርካታ የኑፋቄ እና የስህተት ትምህርቶች ከሚተላለፉባቸው መንገዶች መካከል የብዙኃን መገናኛዎች መሆናቸውን ተጠቅሷል።
ከእነዚህ መገናኛዎች መካከል ደግሞ የቴሌቪዥን እና የማኅበራዊ ሚዲያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።
የሥነ መለኮት መምህሩ ተካልኝም (ዶ/ር) ማኅበራዊ ሚዲያ የፈጠረው ዕድል ከፍ ያለ መሆኑን በመጥቀስ “ከዚህ በፊት አንድ ሰው አለኝ ብሎ በሚያስበው ፀጋ ለማገልገል ሲያስብ የሚጀምርበት የሚፈተንበት፣ የሚፈተሽበት ማኅበረሰብ ነበረ።
“አሁን ግን ከኪሱ አንዳች ገንዘብ ሳያወጣ አኗኗሩ እና የትምህርቱ ጤናማነት ሳይረጋገጥ ራሱን ድንገት ሾሞ በማኅበራዊ ገጾች ውስጥ ራሱን አስተዋውቆ፣ በልበ ሙሉነት እንዲህ ዓይነት አገልግሎት አለ ብለው የሚያስቡ ሰዎችን ማታለል የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሯል።”
መንፈሳዊ ማዕረጎችን የሚሰጠው ማን ነው?
እነዚህ በወንጌላውያን አማኞች ስም የተለያየ ማጭበርበሮችን የሚፈጽሙ ግለሰቦች ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመጥቀስ ባለፈ የተለያየ መንፈሳዊ ማዕረጎችን ሲጠቀሙ ይታያል።
በወንጌላዊ ክርስትና አመለካከት ውስጥ እነዚህ ማዕረጎች ሰጪው ራሱ እግዚአብሔር ነው ተብሎ ነው የሚታመነው ይላሉ ዶ/ር ተካልኝ።
“ነገር ግን ቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ ተገልጋዮች እና መዋቅሩን በአንድ ላይ ደምረን ይህ ሰው ለተሰጠው ስጦታ እውቅና ሰጪ አካል ናት።”
አክለውም ቤተክርስቲያን ግለሰቡ እግዚአብሔር የሰጠውን ተልዕኮ ጤናማነት አረጋግጣ ለዚያ እውቅና የምትሰጥ ናት እንጂ የስሙ ባለቤት አይደለችም ይላሉ።
መጋቢ ጳውሎስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አሰራር እያንዳንዱ ቤተ እምነት የየራሱ ነጻነት (አውቶኖሚ) ያለው መሆኑን ማስታወስ ተገቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህም የተነሳ ይህንን ሹመት እያንዳንዱ ቤተ እምነት ለራሱ አገልጋዮች ይሰጣል።
“ቀጥሎ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ስለሚያገለግሉ . . . የአገልጋይ መቀባበል ስላለ አንዳንዶቹ ጸጋቸው በግልጽ ይወጣል።”
ዶ/ር ተካልኝ በበኩላቸው አንድን ሰው ወንጌላዊ የምታደርገው ቤተክርስቲያን ሳትሆን፣ ወንጌላዊ መሆኑን በሕይወቱ ላይ የሚሰራው ጸጋ ከተመለከተች በኋላ የምታረጋግጥ ናት። ነብይንም እንዲሁም ሐዋርያ እና መጋቢንም በተመሳሳይ መንገድ ነው ሲሉ የመጋቢ ጳውሎስን ሀሳብ ያጠናክራሉ።
ይህ ሥነ መለኮታዊ ዕይታ ግን ክፍተት መፍጠሩን ሁለቱም የሥነ መለኮት አዋቂዎች ይስማማሉ።
ይህንንም ተካልኝ (ዶ/ር) ሲያብራሩ “ሰዎች እኔ አምላክ ሾሞኛል፤ ይህንን ስጦታ ሰጥቶኛል። ግን ሰዎች በአምላክ መንገድ ላይ ቆመው በእኔ ውስጥ የሚሰራውን ጸጋ አልተቀበሉትም እውቅና አልሰጡትም፤ ገፍተውታል ለሚል አመለካከት ክፍተት ይፈጥራል” ብለዋል።
በዚህ ክፍተት ላይ በመንተራስ ሰዎች ተቋማዊ በሆነ መልኩ ቤተክርስቲያን ፈትሻ ትክክለኛነቱን አረጋግጣ፣ አላቸው ተብሎ የሚታሰበውን ጸጋ አጽድቃ ሹመቱን እውቅና ሳትሰጥ ሰዎች በራሳቸው ተነሳስተው የሚፈልጉትን ማዕረግ ለራሳቸው እየሰጡ “እኔ ነብይ ነኝ፤ እኔ ሐዋርያ ነኝ. . . ” የሚሉበት መንገድ መፈጠሩን ይናገራሉ።
“አሁን ግን ችግር እየፈጠሩ ያሉት . . .’ዋን ማን ሊደሮች’ ናቸው። ራሳቸው የቸርቹ ባለቤት፣ ራሳቸውን የሚሾሙት ራሳቸው ናቸው። ተጠያቂ የሚሆኑበት ሌላ አካል የለም” የሚሉት ደግሞ ጳውሎስ ፈቃዱ ናቸው።
በማኅበረ ምዕመናኑም ረገድ በዋነኛነት በተቋም አደረጃጃት እና ተቋሙ ከሚሰጠው እውቅና በበለጠ በዚያ ሰው ውስጥ እየታዩ ናቸው የሚባሉ ምልክቶች ላይ የማተኮር አድልዖ አለ የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ተካልኝ ናቸው።
“አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች የቤተክርስቲያን መሪዎች ሊገፉ ይችላሉ የሚል እምነት ስላለ ማለት ነው። በዚህ መካከል ያለውን ክፍተት በመሃል መጠቀም ለሚፈልጉ ሕዝቡን መነገጃ ለሚያደርጉ ሰዎች በር ይከፍታል።”
ሐሰተኛ ነብያት መለያ ባሕርያት አላቸው?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሥነ መለኮት ምሑራን በአንድ ድምጽ ዋነኛ ባሕሪያቸው የመልዕክታቸው ማዕከል የሚያጠነጥነው የራሳቸውን ሰብዕና በመገንባት ላይ ነው ይላሉ።
ከሌሎች የሃይማኖት መሪዎች በተለየ በሚፈጽሟቸው ድርጊቶች እና በሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ሁሉ የመጨረሻ ግባቸው፣ በምእመኑ ዘንድ መደመምን መፍጠር፣ በዚህ ውስጥ የራሳቸውን ትልቅነት መናገር፣ በመጨረሻም የተገነባውን የራስ ትልቅነት በመጠቀም ለራስ አላማ ገንዘብ ወደ ማካበት መምራት መሆኑን ይስማሙበታል።
በሁለተኛ ደረጃ መልዕክታቸው “በምንም ዓይነት መንገድ ቢለበጥም፣ ዋና ትኩረቱ ገንዘብን ከምእመኑ ኪስ ከመመንተፍ ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ።
“ይህም እናገለግለዋለን ብለው ከሚሉት ማኅበረሰብ መካከል ገንዘብ ያላቸው እነማን ናቸው ብሎ እነዚያን ሰዎች ሆን ብሎ ማጥመድ፣ ይቻላል ብለው በሚያስቧቸው መንገዶች ሁሉ ስለ እነዚያ ሰዎች መረጃ መሰብሰብ፣ የእነርሱን ትልቅነት የሚናገሩ ሰዎች በእነዚህ ሰዎች አካባቢ ማሰማራት የሚያገለግሉትን ሰው አጥምደው ኪሱን ወደ ኪሳቸው መገልበጥ” የሚያሳዩት ባሕሪይ መሆኑን ተካልኝ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ።
ሰው ሃጥያት ሠራ አልሰራ፣ ጥፋት አጠፋ አላጠፋ፣ ግድ የለሽ መሆናቸውን የሚናገሩት የሥነ መለኮት መምህራኑ፣ በሆነ ዓይነት መንገድ የተከታዮቻቸውን ሥነልቦና በመደገፍ የተሰማሩ ናቸው።
በተጨማሪም ምእመኑ ከእነርሱ ጋር ባለው ግንኙነት እና አብሮነት ውስጥ ምቾት እንዲሰማው፣ አጥፍተው እንኳ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው የሚያደርጉ ናቸው ይሏቸዋል።
ሕግ መፍትሔ አለው?
“ማንኛውም የአገልጋይነት ጭንብል ያጠለቀ ሁሉ በአገልጋይነቱ ሽፋን ሌላ ሰው ላይ በደል እየሰራ፣ ሌላ ሰው በሚከሰስበት ጥፋት እርሱ የማይከሰስበት ምክንያት የለም” የሚሉት ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው።
ጥያቄው ግን ብዙ ሰዎች ይህ ዕድል እንዳለ እያወቁ ለምንድን ነው የማይጠቀሙት የሚለው ነው?
ጀመሪያው በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የደረሰባቸውን በደል ለማሰማት ሙከራ ያደረጉ ሰዎች በተደጋጋሚ ማስፈራራት የደረሰባቸው ተበዳዮች አጋጥመውኛል ይላሉ ተካልኝ።
ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ ትል እና ተብለው በወጠምሾች ማሽጠንቀቂያ የተሰጣቸው ተበዳዮች አሉ። “ስለዚህ የፍርሃት ማነቆ አለ ማለት ነው።”
አክለውም “በተበዳይ ልብ ውስጥ የሳሉት ፍርሃት በአብሮነታቸው ዘመን እነዚህን ሰዎች ለማጋለጥ የሞከሩ ሰዎች ሁሉ ክፉ ነገር እንደደረሰባቸው ሲጋቱ ነው ያደጉት፣ ስለዚህ የሆነ ነገር ብንናገር በእኛ፣ በቤተሰቦቻቸን ላይ ተከትሎ የሚመጣው ነገር እጅግ አደገኛ ነው የሚል ፍርሃት አላቸው”
ሌላው ወደ ሕግ ሄዶ አቤቱታ ለማቅረብ ችግር የሚሆነው እነዚህ ሰዎች ማጭበርበራቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ ማቅረብ አዳጋች መሆኑ ነው።
እነዚህን ሐሰተኞች በሕግ ፊት አቁሞ ለማስጠየቅ የሚያስችሉ የተሰጡ ስጦታዎች እና የተደረጉ የገንዘብ ልውውጦች ምንም ዓይነት መስካሪ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የሚፈጸሙ ስለሚሆኑ ማስረጃ ለማቅረብ አዳጋች ያደርገዋል።
በወንጌላውያን ክርስትና አማኞች መካከል ብበደል እንኳ “ወደ ሕግ ይዤ ከምሄድ ለአምላክ ብተወው እና አምላክ በራሱ ጊዜ ፍርዱን ቢሰጥ ይሻላል” የሚል አመለካከት አለ ሲሉ ተካልኝ በተጨማሪ ያስረዳሉ።
እነዚህ እና መሰል ምክንያቶች በአንድ ላይ ተደምረው ወደ ከሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ነገ የሚያደርሱት ተጨማሪ በደል እንዳይገታ መሰናከል መሆኑን የእምነቱ ተከታዮች ይናገራሉ።
ተጠንቀቁ ማለት የማን ድርሻ ነው?
ከአምስት ዓመት በፊት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በ32ኛ መደበኛ ጉባኤው ይህንን ጉዳይ ዋነኛ ጭብጥ አድርጎ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
ከዚህም ባሻገር በዚህ የማጭበርበር ሁኔታ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን በስም በመጥቀስ መግለጫ የሰጠበት ወቅትም አለ።
በቤተክርስቲያን ደረጃም የመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ ስም ጠቅሳ አገለግሎት ላይ እንዳይሳተፉ በይፋ አቋሟን አሳውቃለች።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የሥነ መለኮት ምሑር “ኃላፊነቱ የቤተክርስቲያን ነው” ይላሉ።
ቤተክርስቲያን የተሰሩ ስህተቶችን ለማስተካከል ከምትታገል ይልቅ ትክክለኛውን ዶክትሪን ማስተማር ላይ ማተኮር አለባት ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።
“በዋነኛነት የእውነተኛ አገልጋዮች ሁሉ ድርሻ ነው። ምክንያቱም እውነትን መግለጥ፣ ሐሰትን የመግለጥም ገጽ ስላለው” ያሉት የሥነመለኮት መምህሩ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው።
በተለይ ደግሞ የሙሉ ጊዜያችንን ሰጥተናል፣ ሥነ መለኮት አጥንተን የመመርመር አቅም አለን የሚሉ ምእመናን ሁሉ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉም ያክላሉ።
የወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዝዳንት መጋቢ ጻድቁ አብዶ ኅብረቱ ከሰባት ዓመት በፊት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ባወጣበት ወቅት ጥናት ማድረጉን ያስታውሳሉ።
በጥናቱ ወቅት አንዳንዱ አስተምህሮቱ ልክ አይደለም፣ ልምምዱም ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፣ የሞራል አቋሙም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚፈቅደው ውጪ መሆኑን መለየታቸውን ይናገራሉ።
ሁለተኛው ወገን ደግሞ “ትምህርታቸው ልክ ሊሆን ይችላል። ብዙም በአስተምህሮ ላይሳሳቱ ይችላሉ። እዚህም እዚያም የሚረግጡ ናቸው። ግን ደግሞ በልምምድ የተሳሳቱ ሊኖሩ ይችላሉ” ይላሉ ጻድቁ።
ሌላኛው ደግሞ ትምህርቱ ልክ ሆኖ የሞራል አቋሙ ልክ ላይሆን ይችላል ሲሉም ያክላሉ።
ኅብረቱ ይህንን ጥናት አድርጎ መግለጫ ካወጣ በኋላ ተመክረው ከተጣመመ መስመራቸው የተቃኑ እንዲሁም “ትንሽ የደነገጡ፣ የታረሙም አሉ” ይላሉ መጋቢ ጻድቁ።
በተቃራኒው ደግሞ ምንም የሚከለክላቸው እንደሌለ ያሰቡ፣ ያለ አግባብ እንደተነቀፉ በተጨማሪም እንዲስተካከሉ የጠየቋቸውን “የእግዚአብሔር መንፈስን እና ኃይል እንደማይቀበሉ” አድርገው የተቿቸው መኖራቸውንም ያስታውሳሉ።
መጋቢ ጻድቁ ኅብረቱ ያንን መግለጫ ካወጣ በኋላ የተለያዩ አዳዲስ ልምምዶችን ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
“ወንጌል አማኝ ነኝ ካልክ የመጨረሻው ባለሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ እግዚአብሔር አዲስ ነገር ይሰራል ተዓምር ይሰራል እያልክ ልትሰራ አትችልም።”
እነዚህ ሰዎች የማኅበረሰብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው መመልከታቸውን የሚናገሩት መጋቢ ጻድቁ፣ “በጣም የሚያሳዝነው የተጎዳው ተምሮ ሲወጣ ያልተጎዳው ሄዶ ይገባል” በማለት በዚህ ጉዳይ ሕይወታቸው ምስቅልቅል ያለ፣ ኢኮኖሚያቸው፣ አእምሯቸው፣ ስሜታቸው የተጎዳ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
“ትበለጽጋለህ ብለው ያጯጩሀሉ፤ እርሱ [ምዕመኑ] አይበለጽግም። እነርሱ ግን ራሳቸውን ያበለጽጋሉ” በማለት ምእመናን የላባቸው ፍሬ ያልሆነ ገንዘብ በኪሳቸው፣ በባንክ አካውንታቸው እንደሚገባ እየሰበኩ ማጭበርበሮችን ሲያከናውኑ መመልከታቸውን ይናገራሉ።
እነዚህ የስህተት ልምምዶች “እኛ ወንጌላውያንን አይወክለንም” የሚሉት መጋቢ ጻድቁ፣ ማኅበረ ምእመናኑም ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ተግባር ሲመለከት በግልጽ መቃወም አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።
ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው በወንጌላውያን አማኞች ስም የተመሰረተ የወንጌላውያን ኅብረት (ካውንስል) መኖሩን አስታውሰው ይህ ኅብረት፣ “ገና ማንነቱ ያልጠራ፣ በእንዲህ ዓይነት ሂደት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን አካል አድርጎ ያቀፈ ስለሆነ በጣም ጠንከር ያለ አቋም በቅርቡ ይይዛል የሚል አቋም የለኝም” ይላሉ።
መጋቢ ጳውሎስ በበኩላቸው እነዚህ ተቋማት ስለ ሐሰተኛ ነብያት በይፋ ማሳወቅ፣ ማስተማር፣ ማውገዝ እና ከእኛ ጋር ግንኙነት የላቸውም ብሎ ማጋለጥ እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ይህንን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ከኃላፊነታቸውን መልቀቅ አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ያጠናቅቃሉ።