በዘረመል አርትዖት
በመኮንን ተሾመ
ምርምሩ የጤፍ ምርት ኪሳራምን በ25% ለመቀነስ ያስችላል ተብሏል
ጤፍ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና የዲያስፖራ አባላት ዋነኛ ምግብ ነዉ። አዲስና በከፊል አጠር ያለ የጤፍ ዝርያ በዘረመል አርትዖት ለማዉጣት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም እና በአሜሪካዉ በዶናልድ ዳንፎርዝ የእፅዋት ሳይንስ ማዕከል የዓለም አቀፍ የሰብል ማሻሻያ ተቋም ተመራማሪዎች ትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ የግብርና ምርምር ተቋም መግለጫ አስታዉቋል።
የዘረ-መል አርትዖት ምርምር ፕሮጀክ በጤፍ ላይ የመጋሸብና መሰበር ችግርን ለመከላከል እና በችግሩም ምክንያት የሚደርሰውን የምርት ብክነት በመከላከል የእህልን ምርታማነት ለማሻሻል ያለመ ነው።
የጤፍ አገዳ በተፈጥሮዉ ቀጭን የሆነና በረዘመ/በጋሸበ ቁጥር ፍሬዉ ስለሚከብደዉ ለመታጨድ ያልደረሰዉ ለጋዉ አዝመራ በተለይም በንፋስና በዝናብ የመታጠፍና የመሰበር አደጋ ስለሚያጋጥመዉ ለምርት ሳይበቃ ብዙ ጊዜ የመበላሸት አደጋ ያጋጥመዋል።
በመሆኑም በዘረ-መል አርትዖት/ጂኖም ኤዲት/ genome-editing/ የቁመት ቅነሳ የተደረገላት ጤፍ ወደ 25% የሚደርስ የምርት ኪሳራም ለማስቀረትም አቅም ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል ሲል መግለጫዉ አመልክቷል።
እንደ አዝዕርት ሳይንቲስቶች ገለፃ በጤፍ ላይ የሚታየዉ መጋሸብና በንፋስ ወይም በዝናብ ምክንያት የሚደርስበት መሰበርና መታጠፍም በከፍተኛ ሁኔታ የምርት መቀነስ ከማስከተሉም በላይ ለበሽታ እና ለተባይ ተጋላጭም ያደርገዋል። ይህም የእህሉን የፕሮቲን ይዘት ጭምር መቀነስና ብክለትን በመጨመር ጥራቱ እንዲቀንስ ያደርጋል።
በዚህ የምርምር ፕሮጀክት ከሚሳተፉት ተመራማሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም የባዮቴክ ምርምር ዳይሬክተሩ ዶ/ር ደጀኔ ግርማ፣ እንዳሉት አዲሱ ዝርያ ከምርታማነት በተጨማሪ ጤፍን ለሜካናይዝድ እርሻ ምቹ ያደርገዋል።
እንደ ዶ/ር ደጀኔ ከሆነ እ∙አ∙አ በ2021 የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም ከአሜሪካዉ DDPSC ጋር በትብብር የምርምርና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም በዘረመል አርትዖት የጤፍን ምርታማነት ለመጨመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
በማስከተልም እ.ኤ.አ. በ 2022 በዘረመል አርትዖት የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ለዩናይትድ ስቴትስ የግብርና ዲፓርትመንት የእንስሳት እና የእፅዋት ጤና ቁጥጥር አገልግሎት (USDA-APHIS) ለባዮሴፍቲ ቁጥጥርና ፍተሻ ቀርቧል ያሉት ዶ/ር ደጀኔ ተቋሙም ማመልከቻውን ከገመገመ በኋላም በዘረ-መል የተስተካከለዉና በፊል-አጭር የሆነዉ ጤፍ ዝርያ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ምርምሩ ሊቀጥል እንደሚችል አስታዉቋል ሲሉ አስረድተዋል።
ይህን የጂኖም ኤዲቲንግ ስራ አስመልክቶ የIICI የሬጉላቶሪ ሳይንስ ከፍተኛ ስራ አስኪያጅና የጤፍ ዘረመል አርትዖት የመጀመሪያዉ አለም አቀፍ ምርምር ጽሁፍ አቅራቢ ዶ /ር ጌቱ በየነ ዱጉማ በበኩላቸው ለዳንፎርዝ ሴንተር እንደተናገሩት “እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርና ስራ በሚዘወተርበት ቦታ ነው ያደግኩት እናም ከተሳካልን ይህ ምርምር ለእኛ አርሶ አደሮች ጥቅሙ እጅግ የላቀ እንደሚሆን በተጨባጭ እረዳዋለሁ። ” ብለዋል።
የዳንፎርዝ ሴንተር የዩናይትድ ስቴትስ የግብርና ዲፓርትመንት (USDA) የእንስሳትና ዕፅዋት ጤና ቁጥጥር አገልግሎት ባደረገው የቅድመ ገበያ የሁኔታ ግምገማ በጂኖም ኤዲቲንግ የተሻሻለውና ከፊል ድንክ የሆነ ቁመት ያለው የጤፍ የምርመር ዉጤት በባዮቴክኖሎጂ ቁጥጥር ሂደት እንዲያልፍ በሃገሪቱ ህግ መሰረት (በ USDA የደህንነት ጥበቃ ህግ) አይገደድም።
የ IICI ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዶናልድ ማኬንዚ በዚህ ዙሪያ ሲናገሩ ” በእዉነቱ የUSDA ውሳኔ በጣም የሚያበረታታ ነዉ። ምክንያቱም በጤፍ ላይ የሚከሰተዉን የፍሬ ማቀፊያ መሰባበርን ለመከላከል ፣ የጤፍን ፍሬ የደቃቃነት ይዞታ ለማሻሻል፣ አረምን ለመከላከል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የመሳሰሉ የምርታማነት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥሩ ቅድመ ሁኔታን የሚፈጥር ነዉ።” ሲሉ የገለፁት ዶ/ር ዶናልድ በከፊል ቁመቱ አጠር እንዲል በተደረገዉ የጤፍ ዝርያ ላይ በዚህ አመት በዳንፎርዝ ሴንተር የመስክ ምርምር ግምገማ ይካሄዳል ብለዋል።
ዝርያዉ በመጪዉ ሰኔና ሃምሌ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም የተመራማሪዎች ቡድን እና የአመራር አካላት፣ ከኢትዮጵያ አካባቢ ባለስልጣን የተወከሉ ተቆጣጣሪዎች እና የኢፌዲሪ ፓርላማ የግብርና ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ ሀላፊዎች በተገኙበት ወደ አሜሪካ ሚዙሪ ግዛት በመጓዝ በመስክ ሲተከል በአካል የሚጎበኙ ሲሆን ከአሜሪካ ሳይንቲስቶችና የሰብል ልማት ተቆጣጣሪዎችም ጋር ተገናኝተዉም የሚመክሩ ይሆናል።
በአለማችን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ከፊል ድንክ የሆኑ የስንዴ እና የሩዝ ዝርያዎች በዚሁ የመራቢያ ዘዴዎች በመስፋፋታቸው የእህል ምርትን በመጨመር “አረንጓዴ አብዮት” አስከትለዋል። ይህ እድገት በሃያኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በዓለም ዙሪያ የነፍስ ወከፍ የምግብ አቅርቦትን ከፍ ለማድራግ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል።
ከፊል ድንክ የሆኑና መተመሳሳይ ምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎች በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በአጠቃላይ 99% የሚሆነዉን የስንዴ ምርት በመሸፈን የጎላዉን ድርሻ ይዘዋል።
ጤፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝና በደቃቅነቱ የሚታወቅ እህል ሲሆን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በዋነኛ ምግብነት የሚያገለግልና እስከ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነዉን የህዝቡን የፕሮቲን እና የምግብ ፋይበር ፍላጎት እንደሚያሟላም ይገመታል። ጤፍ ለኢትዮጵያውያን ዋነኛ ምግብ ከመሆኑ በተጨማሪ በሀገሪቱ ውስጥ ላሉ በርካታ አነስተኛ ገበሬዎች ጠቃሚ የገቢ ምንጭም ነው።
ጤፍ በርካታ ጥቅሞች ስላሉትና እና የምግብነት አዘገጃጀቱም ሁለገብ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ እየሆነ እንዲመጣ አድርጎታል። ጤፍ በፕሮቲን፣ በፋይበር ፣ በብረት፣ በካልሲየም እና በማግኒዚየም ማዕድናት እንዲሁም በተለያዩ በንጥረ-ምግቦች የበለፀገ ነው። ሰብሉ ከ“ግሉቶን”-ነጻ ስለሆነም የተለያዬ የጤና እክል ላለባቸዉ ሰዎችም ጥሩ አማራጭ ያደርገዋል። በምእራብ ዩናይትድ ስቴትስ በዋናነት በካሊፎርኒያ፣ ኮሎራዶ፣ ኢዳሆ፣ ኔቫዳ እና ኦሪገን የሚገኘው የጤፍ ምርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጨመረ የመጣው ከግሉተን-ነጻ እና ጤናማ እህሎች ፍላጎት እያደገ መምጣቱንም ማሳያም ነው ተብሏል።