የ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአንድ ዓመት በፊት “ገድዬዋለሁ” ያለው ከፍተኛ የ አል-ሸባብ መሪ በሶማሊላንድ የሽብር እንቅስቃሴ እየመራ ነው ተባለ።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ጷጉሜ 3/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከአል-ሸባብ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆነው ፉአድ መሐመድ ከህላፍ፣ ላስአናዶ በተባለው ግዛት የሽብር እንቅስቃሴ እየመራ ነው ብሏል።
ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ የአል-ሸባብ የቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ፉአድ መሐመድ ከህላፍን ጨምሮ ሦስት የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ገድያለሁ ብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ባለፉት ጥቂት ቀናት ፉአድ መሐመድ ከህላፍ 600 ተዋጊዎችን እየመራ ለአካባቢው ሚሊሻዎች የተቀጣጣይ ነገሮች አሰራር ሥልጠና ለመስጠት እና በአካባቢው ያሉ ተራራማ ቦታዎችን እንዴት የጦር ሰፈር አድርጎ መጠቀም እንደሚቻል ጥናት ለማድረግ ላስአናዶ መግባቱ ተረጋግጧል ብሏል።
በቅጽል ስሙ ሾንጋሌ ተብሎ የሚጠራው ፉአድ መሐመድ ከህላፍ የሶማሊያ እና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው ሲሆን አሜሪካም እርሱን መያዝ የሚያስችል ጥቆማ ለሰጠኝ አምስት ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ስትል ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ከአል-ሸባብ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆነውን ፉአድ መሐመድ ካህላፍን ገድያለሁ ማለቷ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ ነበር።
ከአንድ ዓመት በፊት የአገር መከላከያ ሠራዊት ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው፤ ፉአድ መሐመድ ካህላፍን እና የሦስት ተጨማሪ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መገደልን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፉአድ መሐመድ ካህላፍ ግድያን ይፋ ካደረገ በኋላ ጽንፈኛ ቡድኑ የፉአድ የመገደል ዜና ሐሰት ነው ያለ ሲሆን ምንም እንኳ በገለልተኛ ወገን ትክክለኛነቱ ማረጋገጥ ባይቻልም ፉአድ መሐመድ ካህላፍ የሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ናቸው የተባሉ ንግግሮች በኢትዮጵያ ተገድሏል ከተባለ በኋላ በመገናኛ ብዙሃን ሲወጡ ነበር።
በወቅቱ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ከፉአድ መሐመድ ካህላፍ በተጨማሪ የቡድኑ ቃል አቀባይ ነው የተባለው አብዱላዚዝ አቡ ሙሳ እና የባኩል ዞን እና የኢትዮጵያ ድንበሮች አዋሳኝ ኃላፊ ኡቤዳ ኑር ኢሴ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥቃት መገደላቸውን ተናግረው ነበር።
የሶማሊላንድ መንግሥት በመግለጫው ላስአናዶ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥር፣ የምልመላ ጥረቶች እና የጽንፈኞች ፕሮፖጋንዳ መጨመሩ እጅግ አሳስቦኛል ያለ ሲሆን የጽንፈኞች እንቅስቃሴ ለሶማሊላንድ እና ለአጠቃላይ ሰፊው ቀጠና ስላም እና መረጋጋት ትልቅ ስጋት ነው ብሏል።
የሶማሊላንድ መንግሥት ጎረቤት አገራት እና አጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ በላስአናዶ የጽንፈኞች እንቅስቃሴ ለመግታት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
የአገር መከላከያ እነዚህን ሦስት የጽንፈኛው ቡድን ከፍተኛ አመራሮችን ገድያለሁ ያለው አል-ሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር በመሻገር ጥቃት እየከፈተ በነበረበት ወቅት ነው።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ አል-ሻባብ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑት የሶማሊያ ከተሞች ላይ ጥቃት ከፍቶ የነበረ ቢሆንም በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና በአገር መከላከያ ኃይል ጽንፈኛ ቡድኑ መመከቱ ሲገለጽ ነበር።
የቡድኑ ታጣቂዎች በአንድ ወቅት ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው በመግባት ጥቃት ሰንዝረው በሶማሌ ክልል እና በፌደራሉ ሠራዊት በተወሰደ እርምጃ ከሁለት መቶ በላይ አባላቱ መገደላቸውንም መንግሥት አስታውቆ ነበር።
ቢቢሲ አማርኛ