በመኮንን ተሾመ ቶሌራ (ከአፋር፣ ሰመራ )
ነገ ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ᎐ም በሰመራ ከተማ በቴምር ልማት ዙሪያ አገር አቀፍ ምክክር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል
(ሰመራ ፣ አፋር- ሰኔ 4፣2016 ዓ᎐ም᎐) ፡ የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአፋር ክልል ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረዉን የቴምር ልማት የምርምርና የምርታማነት ችግሮችን ለመቅረፍ ድጋፍ ሊያደረግ መዘጋጀቱን ገለፀ።
ይህ የተገለጸዉ ዛሬ በኢንስቲትዩቱ አሰተባባሪነት ወደ ክልሉ ያመራዉና ከኢንስቲዩቱ ፣ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ፣ ከኢትዮዽያ ግብርና ምርምር ተቋም ፣ ከግብርና ሚኒስቴር ፣ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት እና ሎሎች ከሚመለከታቸዉ አካላት የተዉጣጡ ባለሞያዎች በአፋር ክልል አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች የሚደረገዉን የቴምር ልማት በጎበኙበት ወቅት ነዉ።
የልዑካል ቡድኑን የመሩት የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀይሉ ዳዲ በጉኝቱ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች የሚደረገዉ የቴምር ልማት ለመነሻ ያህል መልካም ቢሆንም አፋር ክልል ካለዉ ቴምር የማልማት አቅም ሲታይ ገና ብዙ የሚጠበቅ መሆነ ጠቁመዋል።
“ በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ የቴምር ልማቱን የምርምርና የምርታማነት ችግሮችን ለመቅረፍ ከአጋር አካላት ጋር ለመስራትና ድጋፍ ለመስጠት የሚያችል ጥናት ለማድረግ ይህንን ጉብኝት አመቻችተናል።” ሲሉ ተናግረዋል።
“መንግስት ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ያሉት ችግሮች ተቀርፈዉ አፋር ክልል በቴምር አምራችነት የሚጠቀሰ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም ክልሉ ከበቂ በላይ በመሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለ ነዉ። ” ሲሉ ዶ/ር ሀይሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር በተያያ በጉብኝቱ የተሳተፉት የኢትዮዽያ የባዮቴክኖሎጂ ማህበር ፕሬዝደንትና የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍሬዉ መክብብ በበኩላቸዉ እንዳሉት አፋር ክልል ባለዉ አቅም በመጠቀም የቴምር ምርትን የላቀ ደረጃ ላይ በማድረስ ኢትዮዽያ ከዉጪ የምትስገባዉን ምትር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስና የህዝባችንን የስነ-ምግብ ደረጃ ማሻሻል ይገባል።
“እስካሁን በዘርፉ ለነበሩት ተግዳሮቶች ምክንያት በመስጠት ሳይሆን ያለዉ ኣቅም ከፍተኛ በመሆኑ ሁላችንም ተረባርበን አፋር ክልልን በቴምር ምርት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ማድረስ አለብን።” በማለት ፕሮፌሰር ፍሬዉ አክለዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ከላይ የተገለፁት ባለድርሻ አካላት ነገ ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ᎐ም በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ ምክክር በማካሄድ በመጪዎቹ ጊዜአት የሚተገበሩ ስራዎችን ይለያሉ ተብሎ ይጠበቃል።