By Africa Demystifier
በትንሽም ሆነ ትላልቅ የገበያ መደብሮች ላይ ያሉ የሻይ ቅጠል አይነቶች ዐይን አዋጅ ያስብላሉ።
በርካቶችም ወደ ኬንያ ሲመጡ እንደ ማስታወሻ፣ ወይም ለዘመድ ለወዳጅ ስጦታ ሻይ ቅጠል ገዝተው ይመለሳሉ።
ኬንያ በዓለም ላይ ስመ ጥር ለሆኑ የሻይ ቅጠል ምርቶች ዋነኛ አቅራቢ ናት።
ዩናይትድ ኪንግደም ሃምሳ በመቶ የሚሆነውን የሻይ ቅጠል ፍላጎቷን የምታገኘው ከኬንያ ነው።
በቅርቡ ግን በእነዚህ የሻይ ቅጠል እርሻዎች ላይ በሚሰሩ ሴት ሠራተኞች ላይ የወሲብ ብዝበዛ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ቢቢሲ በምርመራ ደርሶበታል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ታዋቂ ለሆኑት የሻይ ምርቶች ሊፕተን፣ ፒጂ ቲፕስ እና ለሳይንስበሪ ሬድ ሌብል የሻይ ቅጠል የሚያቀርቡ እርሻዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች እየደረሱ መሆኑን ቢቢሲ ተመልክቷል።
በሁለት የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያዎች ለዓመታት በባለቤትነት በሚተዳደሩ የሻይ ቅጠል እርሻዎች ላይ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በአሰሪዎቻቸው ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዩኒሊቨር እና በጄምስ ፊንላይ እና አጋሮች ኩባንያ ባለቤትነት በሚተዳደሩ እርሻዎች ላይ ቢቢሲ በድብቅ ባደረገው ቀረጻም የአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች አንዲትን ሴት ለወሲብ ሲያስገድዷት ያሳያል። ግለሰቧ ቢቢሲ በድብቅ ሪፖርት እንድታደርግ የላካት ዘጋቢ ናት።
የምርመራ ዘገባው መውጣቱን ተከትሎ ሦስቱ ኃላፊዎች ከሥራ ታግደዋል።
ዩኒሊቨር የተሰኘው ኩባንያም ከ10 ዓመታት በፊት ተመሳሳይ የወሲብ ብዝበዛ ክሶች ቀርበውበት ማንኛውንም ወሲባዊ ትንከሳ ፍፁም አንታገስም የሚል ዘመቻ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ሪፖርት የሚደረጉበት ሥርዓት ዘርግቻለሁ ብሎ ነበር።
ነገር ግን ቢቢሲ አፍሪካ አይ እና ፓናሮማ በጋራ ባካሄዱት ምርመራ ወሲባዊ ትንኮሳዎች ሪፖርት ቢደረጉም ኩባንያው ምንም ዓይነት እርምጃ እየወሰደ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን አግኝተዋል።
የቢቢሲው ጋዜጠኛ ቶም ኦዱላ በሁለቱም ኩባንያዎች ስር ያሉ የሻይ ቅጠል እርሻዎች ላይ ይሰሩ የነበሩ ሴቶችን አነጋግሯል።
- “የወሲብ ብዝበዛ ተጠቂ መሆኔን ለመረዳት ዓመታት ፈጅቶብኛል”20 ጥቅምት 2019
- ባለፉት አስር ዓመታት ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለምን ቁጡ ሆኑ?29 ታህሳስ 2022
- ጺም ስለሚያበቅሉ ሴቶች ሳይንስ ምን ይላል?31 ጥር 2023
ብዙዎቹም በአካካቢው ብዙም ሥራ ስለማይገኝ አለቆቻቸው ወሲብ ሲጠይቋቸው እና ሲያስፈራሯቸው ከመታዘዝ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ነግረውታል። አለዚያ ግን ከሥራ እንባረራለን ብለውታል።
“ልጆች ስላለኝ ሥራዬን ማጣት አልችልም” ስትልም አንዲት ሠራተኛ ተናግራለች።
ሌላኛዋ ሠራተኛ ደግሞ የአንድ የሥራ ክፍል ኃላፊ ከእሱ ጋር ወሲብ ለመፈጸም እስክትስማማ ድረስ ከሥራዋ ታገደች።
“ስቃይ ብቻ ነው። ወሲብ በመፈጸም ብቻ ነው ሥራ የሚገኘው” ትላለች።
ሌላኛዋ ሴት ደግሞ አለቃዋ ከእሱ ጋር ወሲብ እንድትፈጽም ካስፈራራት እና የጠየቀውን ከፈጸመች በኋላ በኤችይቪ እንደተያዘች ለቢቢሲ አስረድታለች።
እየደረሱ ነው ስለተባሉት ወሲባዊ ጥቃቶች ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ የቢቢሲ ዘጋቢ ማንነቷን ደብቃ በሻይ ቅጠል እርሻው ውስጥ እንድትሠራ ተቀጠረች።
ለዚህ ዘገባ ሲባል ኬቲ ብለን እንጠራታለን።
በአንድ አጋጣሚም ኬቲ ጆን ቼቦቾክ የተሰኘ የጄምስ ፊንላይ ኩባንያ ቀጣሪ ለቃለ መጠይቅ ጠራት። ቃለ መጠይቁንም እንዲደረግ ያዘጋጀው በአንድ ሆቴል ክፍል ውስጥ ነው።
ጆን ቼቦቾክ በፊንላይ እርሻዎች ላይ ከ30 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግሏል። በመጀመሪያ በንብረት ተቆጣጣሪነት በመቀጠልም የአንድ ኮንትራት ኩባንያም ባለቤትም በመሆን የሠራው ጆን፣ ቀደም ሲል የቢቢሲው ቶም ኦዱላ ያነጋገራቸው በርካታ ሴቶች “በዋነኝነት ጥቃት አድራሽ” እንደሆነ በተደጋጋሚ አንስተውታል።
ኬቲ ሆቴሉ ውስጥ ከገባች በኋላም ጆን ግድግዳ ላይ አስጠግቷት እንድትነካው እና ልብሷን እንድታወልቅ ጠየቃት።
“ገንዘብ እሰጥሻለሁ፣ ከዚያም ሥራ እሰጥሻለሁ። ረድቼሻለሁ አሁን ደግሞ እርጂኝ” አላት።
“ቀላል ነው። እንተኛለን ከዚያም ጨርሰን መሄድ ነው። ሥራም ትጀምሪያለሽ” ይላት ጀመረች።
ኬቲ ግልጽ በሆነ ቋንቋ እንዳልተስማማች ተናገረች። ግለሰቡ ሊያሳምናት ቢሞክርም ልትስማማ ስልቻለች በመጨረሻም ተስፋ ቆረጠ። እናም ለደኅንነቷ ሲባል በአካባቢያዋ ተሰማርተው የነበሩት ሠራተኞች ስልክ ደውለው እንደምትፈለግ በመጥራታቸው ልታመልጥ ቻለች።
“በወቅቱ በጣም ፈርቼ እና ደንግጬ ነበር። በግለሰቡ ስር የሚሰሩ ሴቶች በምን ያህል የከፋ ሁኔታ ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ መረዳት ቀላል ነው” ስትል ኬቲ ተናግራለች።
ጄምስ ፊንላንይ ኩባንያ ቢቢሲ ስለ ግለሰቡ የወሲብ ብዝበዛ ክሶች ምላሽ እንዲሰጠው ከጠየቀው በኋላ ወዲያውኑ ከሥራ እንደታገደ አስታውቋል።
ኩባንያው በተጨማሪ ስለ ግለሰቡ ድርጊት ለፖሊስ ሪፖርት እንዳደረገ እና በኬንያ ባለው እርሻው ውስጥ ምን ያህል ስር የሰደደ ወሲባዊ ጥቃት ስለመኖሩ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ኬቲ ለዘገባው በሚል በዩኒሊቨር እርሻ ቦታ በምትሰራበት ወቅትም ወሲባዊ ትንኮሳዎች አጋጥመዋታል።
በአንዲት ዕለት ኤርሚያስ ኮስኬ የሚባል የአንድ ክፍል ሥራ ኃላፊ ዩኒሊቨር የትኞቹንም ወሲባዊ ትንኮሳዎች እንደማይታገስ ለአዳዲስ ሠራተኞች ሲናገር ኬቲ በስፍራው ነበረች።
የኩባንያውን ፖሊሲ ካሳወቀ በኋላ ምሽቱን በሆቴሉ መጠጥ ቤት እየተዝናኑ እንዲያሳልፉ ከጠየቃት በኋላ፣ ከእሱ ጋር ወሲብ እንድትፈጽም ሊያሳምናት እና ሊገፋፋትም ሞክሯል።
ኬቲ በእርሻው ውስጥ በአረም ነቃይነት ሥራ ተመድባ ነበር። በእርሻው ውስጥ ያለው ሥራ በጣም አልፊ፣ አሰልቺ እና አድካሚ ሲሆን፣ በሳምንት ስድስት ቀናት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በርካታ ሴቶችም ወደ ሌላ ሥራም እንዲዛወሩ ይጠይቁ ነበር።
በስፍራው ተቆጣጣሪ የነበረው ሳሙኤል ከእሱ ጋር ወሲብ የምትፈጽም ከሆነ ወደ ቀላል ሥራ እንደምትዛወር ነገራት።
ኬቲ የደረሰባትን ወሲባዊ ትንኮሳዎች ለሚመለከታቸው የዩኒሊቨር ኩባንያ ኃላፊዎች ሪፖርት ብታደርግም የተሰጣት ምላሽ “በአቋምሽ ጽኚ፣ ሰውነትሽን ለሥራ በሚል አሳልፈሽ አትሽጪ” የሚል ነው።
የትንኮሳ ድርጊቱን በፈጸሙ አለቆቿ ላይ የተወሰደ እርምጃ መኖሩን ለማወቅ ክትትል ብታደርግም ምላሽ የሚሰጣት አላገኘችም።
ዩኒሊቨር ደረሱ በተባሉት ወሲባዊ ትንኮሳዎች “በጣም እንደተደናገጠ እና እንዳዘነ” ገልጿል።
ቢቢሲ በምስጢር ቀረጻ ላይ እያለ ኩባንያው በኬንያ ያለውን ድርሻውን ሸጠ።
አዲሱ ባለቤት ሊፕተን ቲ ኤንድ ኢንፊውዥንስ ትንኮሳውን የፈጸሙትን ሁለቱን ሥራ አስኪያጆች ወዲያውኑ ማገዱን እና “ሙሉ እና ገለልተኛ ምርመራ” እንዲደረግ ማዘዙን አስታውቋል።
ፓናሮማ ባደረገው ምስጢራዊ ምርመራም ለፒጂ ቲፕስ እና ሊፕተን ሻይ፣ ሻይ ቅጠል በሚያመርቱ እርሻዎች ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች ሥራቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ከአለቆቻቸው ጋር ወሲብ እንዲፈጽሙ ግፊት እንደሚደረግባቸው አጋልጧል።
ኤርምያስ ኮስኬ ቢቢሲ ስለ ትንኮሳዎቹ ቢጠይቀውም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል። ሳሙኤል ይቤ በበኩሉ የቀረበበትን ክሶች ፍጹም ሐሰት ነው ሲል ክዷል።
ጄምስ ፊንላይ እና አጋሮቹ ለሳይንስበሪና ቴስኮ ሱፐርማርኬቶች እንዲሁም ለስታርባክስ የኬንያን ሻይ ያቀርባሉ።
ቴስኮ ክሱን እጅግ አጥብቆ እንደሚከታተለውና “ጠንካራ እርምጃዎች” መወሰዳቸውንም ለማረጋገጥ ከፊንላይ ጋር በቋሚነት እየተወያየ መሆኑን ገልጿል።
ለቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ምላሽ የሰጠው ሳይንስበሪ በበኩሉ “እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ ክሶች በአቅርቦት ሰንሰለታችን ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም” ብሎ ነበር።
ኩባንያው እንደገና የተሻሻለ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በዚህም “ሠራተኞችን ለመጠበቅ ጠንከር ያለ እርምጃ እንወስዳለን” ብሏል።
ስታርባክስም እንዲሁ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ሁኔታው “በጣም እንዳሳሰበው” በመግለጽ በኬንያ ካለው ጄምስ ፊንላይ እና አጋሮቹ ኩባንያ ማንኛውንም የሻይ ቅጠል ግዢ በማቋረጥ “አፋጣኝ እርምጃ” ወስጃለሁ ብሏል።
የኬንያ መንግሥትም በቢቢሲ የምርመራ ዘገባን ተከትሎ በሻይ ቅጠል እርሻ ሠራተኞች ላይ ይፈጸማሉ የተባሉት ድርጊቶች በእጅጉ እንዳሳሰቡት በመግለጽ፣ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ አርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል። ቢቢሲ