ፕራይም ሚዲያ(አዲስ አበባ)_የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዝግጅቱን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የኃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች በበኩላቸው በዓሉ ኃማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በዚሁ ጊዜ፤ ቤተ-ክርስቲያኗ በዓሉን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ማድረጓን ተናግረዋል።
በበዓሉ አከበባር ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮች ተለይተው አስፈላጊው ውይይት የተካሄደባቸው መሆኑን ጠቁመው የጋራ ግብረ ኃይሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ምዕመናን ኃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን ተረጋግተው እንዲያከናወኑም ቤተ ክርስቲያኗ ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ጠቁመዋል።
በቤተ-ክርስቲያኗ የስብከተ ወንጌል መመሪያ ኃላፊ ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ በበኩላቸው የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ ሥርዓት ባሻገር የአገር ገጽታ የሚገለጽበት ነው ብለዋል።
የበዓሉን ሰላማዊነት ለማስጠበቅም የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በአምስት ቀጠና በመክፈል እስከ 10 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥነ-ምግባር ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የቤተ-ክርስቲያኗ የሕግ ክፍል መመሪያ ኃላፊ አባ ገብረሥላሴ ጌትነት፤ ለበዓሉ ስኬታማነት ዐብይ ኮሚቴና 14 ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።
ኮሚቴዎቹም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው በዓሉ በድምቀት እንዲከበር በመናበብ እየተሰራ መሆኑም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፤ የዓለም ቅርስ የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ፤ የመስቀል ደመራ በዓል ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ በመላው አገሪቱ እንዲከበር የጋራ ግብረ ሃይሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር የሁሉም ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው የኃይማኖት አባቶችም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ መከበር እንዳለበት ገልጸው ከዚህ ባለፈ ሌሎች ፍላጎቶችን ማንጸባረቅ እንደማይገባም አሳስበዋል።
ምንጭ:-ኢዜአ