የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ 99 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን እና ቀሪ የግድቡን የግንባታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅም 50 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ መናገራቸዉን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጽፏል።
“በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተካሒዷል።
በውይይቱ ላይ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንደገለፁት ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት ውስጥ የ10 ነጥብ 65 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት ተጠናቋል።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 99 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 79 በመቶ መድረሱንም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።
እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለፃ የውሃ ማስተላለፊያና መቆጣጠሪያ የብረታብረት ሥራዎች አጠቃላይ አፈፃፀም 90 በመቶ ተከናውኗል።
እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም ድረስ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ 191 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ቀሪ የግድቡን የግንባታ ሥራዎች ለማጠናቀቅም 50 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የኮንትራት ማሻሻያ መደረጉ፣ የተጣበበ የፕሮጀክት ጊዜ ሰሌዳና በግንባታ ወቅት በግድቡ መሠረት ላይ ያጋጠመ ልል ድንጋይ መኖሩ እንዲሁም የልምድ ማነስ እና የጥራትና ልኬት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
በግድቡ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ አመራር እስከ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ድረስ የመዋቅር ለውጥ ተደርጓል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ሥራ ተቋራጮች ከመቅጠር ጀምሮ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻች መደረጉንም ተናግረዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል አምባሳደር ረታ አለሙ እንደገለፁት የፕሮጀክቱን ግንባታ ከማፋጠን በተጓዳኝ ግድቡ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሚሳይ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ ነው።
የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት ሀገራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በመላው ህዝባችን ተሳትፎና በመንግስት ክትትልና ድጋፍ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት 13 ዓመታት ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የገለፁት ዳይሬክተሯ በአሁኑ ወቅትም እስከ 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል።