የአባይ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ዛሬ ማለዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ኢትዮጵያውያን ተባብረን በመሥራታችን ፈጣሪ ረድቶናል። በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በጸሎታቸው በሥራው ውስጥ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ይህ ኅብረታችን በሌሎች ጉዳዮቻችንም ሊደገም ይገባዋል” ብለዋል።
“ብዙ ፈተና ነበረው፤ ወደኋላ እንድንመለስ ብዙ ተጎትተን ነበር። በውስጥ ፈተና በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል” ሲሉም ነው የገለጹት።
የዳገቱ ጫፍ ላይ ደረስን እንጂ ዳገቱን ወጥተን አልጨረስነውም። በቀጣዩ ጊዜ ያቀድነውን አጠናቅቀን ፈጣሪን እንደምናመሰግን እምነቴ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለግድቡ የምናደርገውን ማናቸውንም ድጋፍ እስከ ፍጻሜው እንድንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ አደራ እላለሁ ሲልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።