በመኮንን ተሾመ ቶሌራ (የሳይንስ ጋዜጠኛ) mokish03@gmail.com
በሀገራችን ቀደምትና አንጋፋ የሆነዉ የአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ በ1950 ዓ.ም. ‟የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ /University College of Addis Ababa/” በሚል ስም ተቋቁሞ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ኮሌጆችን ማለትም የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በአዲስ አበባ፣ የጤና ኮሌጅ በጎንደር፣ የእርሻ ኮሌጅ በአለማያ፣ እንዲሁም የህንጻ ስራ ኮሌጅ በአዲስ አበባ አስፋፍቶ ለሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ፋና ወጊ የሆነ ስራ መስራቱ ይታወቃል።
ተቋሙ በኃላም እ.አ.አ በ1961 ዓ.ም አንድ የነገረ መለኮት ኮሌጅን በማካተተ ‟ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በመባል ተቋቋመ። ለዩኒቨርሲቲዉ መጠናከርና ማደግ በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ‟የገነተ ልዑል‟ ቤተ-መንግሥታቸዉን ለትምህርት ተቋሙ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ በርካታ ድጋፎች መበርከታቸዉ እንደዋነኛ ምክንያት ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ በረጅም የአገልግሎትና የስራ ዘመኑ በርካታ ዜጎችን አስተምሯል ፣ የምርምር ተግባራትን አካሂዷል ፣ በሀገሪቱ የማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን መርቷል እናም ለሀገራችን ሁለንተነዊ እድገት ያበረከተዉ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለዚህ እዉነታ የተቋሙ ምሩቃን የሆነዉን ጨምሮ አብዛኛዉ የሀገራችን ዜጎች የሚያዉቁትና የሚያደንቁት ሃቅ ነዉ።
በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወሳኝ የመንግስታት ለዉጥና ህዝባዊ የአቢዮት ንቅናቆዎች ወቅት በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴዎችን የመሪነት ስፍራም አለዉ። የሀገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይመሩ የነበሩ ግለሰቦች እና ትላልቅ ባለስልጣናት በአብዛኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውጤቶች ናቸው፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካለዉ ልምድና ግዙፍነት አኳያ በርካታ አሰተዋፆዎችን አሁንም መጠበቁ አይቀርም። በተለይም በዘመራችን ትልልቅ ተቋማት በዋነኝነት ከሚሰሩት ሰራ በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰሩ ወይም የማህበራዊ ሀላፊነታቸዉን አንዲወጡ ይጠበቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲዉ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸዉ ያለዉን የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ካለዉ ልምድ አንፃር በቂ ካለመሆናቸዉም በተጨማሪ በአግባቡ የታቀዱና የተደራጁ አለመሆናቸዉን በረካቶች ሲገልፁ ይሰማል።
የከፍተኛ ትምህርት የማህበረሰብ አገልግሎት ምን ማለት ነዉ ?
በመሰረቱ ዩኒቨርሲቲዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዋነኝነት ሶስት ተገባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። እነሱም ማስተማር ፣ የምርምርና ማማከር ስራ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎትን ማከናወን ናቸዉ። ይሁንና ተቋማት የማስተማር ስራ ላይ ብቻ በማተኮር ለምርመር ሰራዎች በተለይም ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ሲሆን እናያለን።
እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ትልልቅ ተቋማት የሚያደረጉተ አሰተዋፅኦ በሀገር አቀፍ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲሆን የሚጠበቅ ቢሆንም እንደማንኛዉም የቢዝነስና የትምህርት ተቋም ቅድሚያ የሚሰጡት አጠገባቸዉ ላለ ማህበረሰብ ነዉ። ከዚህ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ምን ፈየደ ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ወደድኩ።
የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ ተጠያቂነትና ግልፀኝነት
በመሰረቱ አንድ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጋር ያለውን የጋራ ትብብር ለመደገፍ ጥረት ያደርጋል ሁለቱም ወገኖች በመማር እና በመማር እኩል አጋር እንደሆኑ እንዲረዱ ያደርጋል። ከተማሪዎችም ከማህበረሰቡ ጋር አብሮ ለመስራት ይተጋል።
ዩኒቨርሲቲና የምርምር የቋማት የሚሰሩት ለማህበረሰብ ጥቅም እንደመሆኑና ለምርምር የሚያገኙትም ገንዘብ ከህዝቡ የሚመነጭ ወይም በህዝቡ ስም ከተባባሪ አካለት የሚገኝ ስለሆነ ማናቸዉም የምርምር ፕሮጀክቶች ከሀሳብ ማመንጨት እሰከ መጨረሻ ትግበራ ድረስ የህዝብ ተሳትፎና ይሁንታ ማግኘት አለበት። ስለዚህ ማህበረሰብን በሚኖሩ ፍላጎቶችና ቅድሚያዎች ዙሪያ ለዉሳኔ ማሳተፍ ያስፈልጋል። ማህበረሰቦች የሚያስፈልጋቸዉ የምርምር ሰራዎች በተመራማሪዎች ተመርጦ የሚሰጣቸዉ ሳይሆን እራሳቸዉ የመረጡተና የተሳተፉበት መሆን ይገባቸዋል።
በምርምር ሰራዎች ዙሪያ የማህበረሰብን ተሳትፎ በተመለከተ የሳይንስ ጋዜጠኞችና ኮሙኒኬተሮች ሚና ከፍ ሊል ይገባል። ባለንበት ዘመን ህብረተሰቡ በምርምር ስራዎቸ ዙሪያ የመሳተፍ ሙሉ መብት እንዳላቸዉ በመገንዘብ ይህንኑ መከታተል ይገባል።
ከምንም ነገር በላይ የሚሰሩ ምርምሮች ሞያዊ ስነ—ምግባርን (Professional Ethics) ያሟሉ መሆናቸዉን ጋዜጠኞችና ማህበረሰቡ ማከታተል ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለምርምር ተግባራት የሚመደቡ በጀቶችም ቀላል የሚባሉ ባለመሆናቸዉ ተቋማቱም የተመደበላቸዉን ገነዘብና አፈፃፀማቸዉንም ማየት ይገባል።
በማህበረሰብ አገልግሎት በማህበረሰቡ የተለዩና የተማሪዎችን ፍላጎት የሚያሟሉ ማህበረሰብን መሰረት ያደረጉ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ ያደርጋል። እንዲሁም ጥራት ያለው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ይፈጥራል ይህም በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በሰራተኞች እና በሰፊው ማህበረሰብ መካከል ያለውን ሽርክና ያካትታል።
ከማህበረሰብ አገልግሎት አንፃር የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ
ባደጉ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ከአጋሮቻቸዉ ጋር በመተባበርና ከሰራተኞች ፣ ከማህበረሰብ አጋሮች እና ተማሪዎች ጋር በመሆን ፕሮጀክቶችን እንዲዘጋጁና እንዲተገበሩ ያደርጋሉ ።
ያላቸውን የምርምር አቅም ፣ ፋይናንስ ፣ የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ ለማህበረሰብ አገልግሎት ያውላሉ። መምህራኖቻቸው ፣ ተማሪዎቻቸውና ሌሎችም በበጎ ፈቃደኝነት /Voluntarism /ላይ እንዲሳተፋ ኘሮግራሞችን በመቅረፅ ማህበረሰቦቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።
ተጠያቂነትን በተመለከተ የተማሪዎች አገልግሎትና ፕሮጀክቶች ግቦች እንዲሁም አላማዎች በግልፅ ይገለፃሉ እና የእያንዳንዱ አጋር ሚናዎች እና ኃላፊነቶችን ለይተዉ ያስቀምጣሉ።
በዩኒቨርሲቲዎች እንቅስቃሴዎች የማህበረሰቡ አባላት በውይይቱ እና በውሳኔ አሰጣጡ ላይ የመሳተፍ እድል ሊኖራቸው ይገባል፣ እንዲሁም የማህበረሰብ አባላትንም የማወያየትና የማሳተፍ ሃላፊነት አለባቸው። ነዋሪዎች የማህበረሰቡ ችግር ዙሪያ እውቀትና ልምድ አላቸው። በዩኒቨርሲቲዎች የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች በዜጎች ተሳትፎ መፅደቅ ይኖርባቸዋል ።
የማህበረሰቡን አባላት በተሳትፎ ሂደቱ ማዳመጥ፣ ማወያየት፣ ማማካከር ከማስፈለጉም በላይ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉ ማደረግ ያስፈልጋል ተብሎ ይታመናል። ስኬታማ የማህበረሰብ ተሳትፎ በማህበረሰቡ ውስጥ ግንኙነቶችን ይገነባል ይህም በመጨረሻም የማህበረሰቡን ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክር እና አዳዲስ የአመራር ባህልን ያዳብራል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የየማህበረሰብ አገልግሎት ሙከራዎች
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምንጮች እንደምንሰማዉ ዩኒቨርሲቲው በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን በመሰጠት ላይ ይገኛል። እንደ ምንጮቹ ከሆነ ከአገልግሎቶቹ መሃል ሙያን ማዕከል አድርገው የሚሰጡ አገልግሎቶችና የምርምር ውጤቶችን ማስተላለፍ መሆናቸውን የጠቁማሉ።
በአንድ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ለሚዲያ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ኀብረተሰቡን የምርምር ግኝቶች ተጠቃሚ እያደረገ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪ ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከርም ተማሪዎች የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ ነውም ብለዋል። በአገሪቱ የሚዘጋጁ ፖሊሲዎች ላይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳትፎ የጎላ መሆኑን የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር ጣሰው በዩኒቨርሲቲው ባለቤተነት የተያዙ ላብራቶሪዎችም በአዲስ አበባ ለሚገኙ መምህራን በራቸዉነ ክፍተ አደርገዉ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እነደሚያግዙና በነፃ ስልጠና እነደሚሰጡ አስረድተዋል።
በህክምና ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነፃ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል እንዲሁም የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ባሉ ሆስፒታሎች በመዘዋወር ህክምና እንደሚሰጡ ሀላፊዎቹ የናገራሉ። ከአዲስ አበባም ዉጭም የኀብረተሰብ የጤና ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን በእንስሳት እንክብካቤና ክትባት ዙሪያም ትምህርት ይሰጣል ሲሉ ያስረዳሉ። የዩኒቨርሲቲው መምህራንም በመገናኛ ብዙሃን የጤና ትምህርት የሚሰጡ ሲሆን በተጨማሪም አቅም ለሌላቸው ዜጎችም ነፃ የህግ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ይነገራል።
ዩኒቨርሲቲዉ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ትኩረት መስጠት ይገባዋል
ከላይ እንደጠቀስኩት ከየማህበረሰብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙም ሆነ በሌላዉ አለም ያሉ የከፍተኛ ትምህርትና የቢዝነስ ተቋማት ቅድሚያ የሚሰጡት በቅርበት ለሚገኘዉና መቀመጫቸዉ ላደረጉት ማህበረሰብ ነዉ። ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ምን አስተዋፅኦ እንዳደረገ መመርመሩ ተገቢ ይሆናል። ስለዚህ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ቅድሚያ ሰቶ መስራት አለበትካልን ከተማዋ ከዩኒቨርሲቲዉ የምትጠብቀዉ ደጋፍ ምን ምነ ሊሆኑ እንደሚችሉ መለየቱ ጠቃሚ ነዉ።
የከተማዋ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች
በመሰረቱ አዲስ አበባ እንደማንኛዉም የታዳጊ ሀገር ከተማ በርካታ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ያሉባት ከተማ ነች። በርካታ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አዲስ አበባ ከፈተኛ ድህነት፣ ስራ አጥነት ፣ የጤናና የትምህርት ችግሮችና ሌሎችም ችግሮች ያሉባት ከተማ ነች። በተጨማሪም የተፈጥሮ አደጋዎች ማለትም የአየር ንብረት ጋር ፣ ጎርፍ ፣ ድርቅ ፣ የሙቀት ሞገዶች እና ቅዝቃዜም ሌሎች ከተማዋን የሚመለከቱ ችግሮቸ ናቸዉ። በተለይም የጎርፍ አደጋ የከተማዋ ቁጥር አንድ የተፈጥሮ አደጋ መሆኑ ይታወቃል። ፖለቲካዊ ችግሮችን በተመለከተም አሁን የሚታየዉን ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ዙሪያ ዩኒቨርሲቲዉ ከማንኛዉም የፖለቲካ ሀይል እራሱን ነፃ በማድረግና የአካዳሚክ ነፃነቱን (Academic Freedom) በፅኑ በመጠበቅ የተለያዩ ሀሳቦችን በማመንጨት መፍትሄ እንዲገኝ ምሁራን አቅማቸዉን እንዲጠቀሙ ማመቻቸት ይኖርበታል።
ከነዚህ የከተማዋ ችግሮች አንፃር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለይ በድህነት ቅነሳ ፣ ለወጣቶች ስራ ፈጠራና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ማፈላለግ ስራ ላይ ማተኮር ይገባዋል። እንዲሁም ባሉብን የፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያም ጭምር የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋት የራሱን አሰተዋፅኦ ሊያደርገ እንደሚደባ አሙን ነዉ።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ምን ያህል የአንጋፋዉን ዩኒቨርሲቲና የሌሎችንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅም እየተጠቀመ እንደሆነ የሚገለፅ ነገረ ባይኖርም አስተዳደሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተማዋን መደገፍ አንዱ ተቋማዊ ‟የህበረሰብ አገልግሎት” እና የማህበራዊ ሀላፊነቱ እነደሆነ በመረዳት በታቀደና ዘላቂነት ባለዉ መልኩ በመተባበር ሊሰራና ከተማዋ ያሉባትን ችግሮች ሊቀርፍ ይገባል።