ይህንን የተረዳሁት ዛሬ ጠዋት እ.አ.አ. December 11 ቀን 2023 ዓ.መ. ነው። ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ ኬፕታውን ደቡብ አፍሪካ በሚበረው የበረራ ቁጥር ET847 ለመሳፈር አየር ማረፊያ ደርሼ ለመሳፈር በምሞክርበት ወቅት ነበር።
በወቅቱ በሰዓቴ ደርሼ ፖስፖርትና ትኬቴን ለሚመለከታት የአየር መንገዱ የትኬት አገልግሎት ሰራተኛ ሳሳያት “ወዴት ነው የምትሄደው ?” ብላ ስትጠይቀኝ ። ወደ ኬፕ ታውን መሆኑን ስነግራት ከዚህ በፊት መሄድ አለመሄዴን ጠይቃኝ የሄድኩበትን አሮጌ ቪዛ እንዳሳያት ጠየቀችኝ። እኔም በምላሹ አሁን የያዝኩት አዲስ ፖስፖርት መሆኑንና ነገር ግን የቀድሞ ፖስፖርቴ ላይ የደቡብ አፍሪካ ቪዛ እንዳለኝ በእምዬ ማሪያም ምዬ ነገርኳት።
ቀጠል አድርጌም “በአዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ማመልከቻየን አገላብጦ መርምሮ (ስራው ስለሆነ/ ህጋዊ ቪዛ ሰቶኝ ሲያበቃ አንቺና መስሪያ ቤትሽ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ እርጎ ዝንብ ምን ጣልቃ አስገባችሁ እዚህ ውስጥ።” ብዬ ለወትሮው የምወዳቸውን የአየር መንገዱን ሰራተኞችና መስሪያ ቤታቸውን መረር አድርጌ ጠየኩ።
እሷም አይ እንግዲህ ሻንጣህን ይዘህ ወደኋላ ሂድልኝ “ምርመራ እናደርጋለን” እሱንም እኔ ሳልሆን የኔ አለቆች ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ሲመጡ እነሱ ናቸው የሚመስኑት ብላኝ ወደኋላ እንዳፈገፍግ አዘዘችኝ። የአየር መንገድ ሰራተኞችን የማውቃቸው ለኔ ሲታዙ እንጂ እነሱ ሲያዙኝ አጋጥሞኝ ስለማያቅ ግራ ገባኝ። በዛ ላይ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ያረጋገጠልኝ የመንቀሳቀስና የመዘዋወር መብት ጥያቄ ውስጥ ገባብኝ።
እናም ደግሜ በንዴት “እዛ ማዶ ያሉት የኢሚግሬሽን እና የደህንነት ሰዎች ምን ስርተው ሊበሉ ነው ? እናንተ ምርመራ ውስጥ ከገባችሁ። አንኳን እናንተ እነሱም በአግባቡና በህግ ካልሆነ የመንቀሳቀስ መብቴን ሊከለክሉ አይችሉም። ነገር ግን የፀጥታና የደህንነት ሀይል ስለሆኑ እኔን የመጠየቅና የመመርመር መብት አላቸው።” አልኳት።
“አይ አንድ ሰው በኛ አየር መንገድ ሄዶ ደቡብ አፍሪካ ቢጠፋ እኛ ነን የምንጠየቀው ቅጣትም አለብን። ” አለችኝና “ለማንኛውም አንድ አስር ደቂቃ ጠብቅ አለቃዬ መቶ ጉዳይህይ አይቶ ይወስናል።” አለችኝ። ነገሩ ቢያናድደኝም በትእግስት ልጠብቅ ወሰንኩ።
እናም 10 ደቂቃ ያለችው 20 ደቂቃ አለፈ። አለቃውን መጠባበቄን ቀጥያለሁ። ተመሳሳይ ነገር የገጠማቸው ሰዎች ግራ በመጋባትና በጭንቀት እኔን ይመለከታሉ ፣ ይሰማሉ። እኔ ግን ሁል ጊዜ በመስሪያ ቤቶቼ ያላግባብ የሚናገሩኝን አለቆቼን ፣ በመንገድ ላይ መኪና እንዳናቆም አስፋልት ላይ ብረት እያስበዬዱና እያቆሙ ህግ የሚጥሱትን ፣ ያላግባብ መኪና እያሽከረከረ የሚበጠብጠውን እና የመሳሰሉት ሲያጋጥሙኝ እንደምከራከረው ሁሉ በቦታው የደረሰውንና ወፍራም የሳይት መነፅር ያደረገውን “አለቃ” መሞገት ጀመርኩ።
የምን የማናውቀው ፖሊሲ መጣ አየር መንገድ ሰውን መርምሩ የሚል ? አልኩት። “እሷ ፖሊሲውን ስለምታውቅ ነው የጠየቀችህ። የተጠየከውን መልስ።” አለኝ።
እኔም “እሷንበግል መቃወሜ አይደለም። እናንተ እንደ አየር መንገድ የኢሚግሬሽን ስራ ውስጥ ገብታችሁ ምን አጨቃጨቃችሁ። ደንንተ ስራ ሌላ። ይሄ ጭቅጭቅ ለስማችሁ ጥሩ ስላልሆነ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር ተነጋግሮ ስራውን ለኢሚግሬሺን ቢሰጥ /መሰጠት ካለበት/ እናንተ ወደ ተፈጥሮአዊ ስራችሁ ፈገግታችሁ ብትገቡ ጥሩ ነው ብዬ ስለማስብ ነው።” አልኩትና።
ከኢሜሌ ላይ ያገኘኋቸውኝ መረጃዎች – ከዚህ በፊት የተጓዝኩትን ትኬት ፣ ከዚህ በፊት የደቡብ አፍሪካ የሳይይስና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የፃፈልኝን ምስጋና እና አሁን የተጋበዝኩበትን ደብዳቤ እያሳየሁት እያለ ሌላ የሱ ባልደረባ መቶ ሰላምታ ሰቶኝ በአይን የሚያውቀኝ ተደጋጋሚ የአየር መንገዱ ደንበኛ መሆኔን ሲገልፅ “እሺ ስራለት” ብሉ መብቴን መልሶ ሰጠን። እኔ ግን አየር መንገዱ ከዚህ ቢወጣ ምክሬ መሆኑን በድጋሚ ጠቅሼለት ተለያየን።
የሚገርመው የአየር መንገዱ ሰራተኞች ለተፈጠረው ነገርና ላደረሱብኝ መንገላታት ይቅርታ ሊጠይቁም አልሞከሩም። ይሁንና እዛዉ አካባቢ ካለ ሰዉ እንደሰማሁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በህግ ባልተሰጠው ሰልጣን ወደ ደቡብ አፍሪካ እና የብራዚሏ ከተማ ሳኦፖሎ የሚጓዙ መንገደኞችን በ”ምርመራ” እና በጥያቄ እያስጨነቁ ይገኛሉ።
ኬንያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ታንዛኒያ ….. እና ሌሎች የደቡብና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ቪዛም ጥያቄም የለባቸውም።
የኔዋ የ”ጥንታዊ ሀገር” ፣ አፍሪካ ህብረትን ያቋቋመች ፣ ማንዴላን ያሰለጠነች ….የ”ታላቋ” ሀገር የኢትዮጵያዊ ልጆች ግን የሰው ፊት እየገረፈን ፣ ከቦታችን ዝቅ ብለን ፣ በየሀገሩ አሳዳድ በዝቶብን።
አየር መንገዳችን “ስደተኛ እንዳታመጣብን” እየተባለ እያየን ተቀምጠናል። ጎበዝ እኔ በበኩሌ የሰውን መብት አከብራለሁ መብቴን ደግሞ በሚገባ አስከብራሁ። ነገር ግን የሀገሬ ሰው ሲንገላታ እና ሲሳቅ ማያት ግን እጅጉን ያስቆጨኛል።
አያስቆጭም ጎበዝ ? እርስ በርስ እየተናጨኝ ከክብራች ዝቅ አልን እኮ !!!
ምህረቱን ስላሴዎች ያቅርቡልን !!!!