በዲላ ዩኒቨርስቲ የምግብ ሳይንስ እና ኒውትሪሽን ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ይሁኔ አየለ፣ በአንድ ቦታ ሆኖ በተለያየ መድኃኒት ከደለበ በሬ ይልቅ በተፈጥሮ ሳር እየተመገበ እና እያረሰ ያደገን በሬ ለሥጋው ጤንነት ተመራጭ መሆኑን ያስረዳሉ።
ዶ/ር ይሁኔ አየለ ከሥጋ ስለሚገኙ ንጥረ ምግቦች ሲያብራሩ በቅድሚያ ፕሮቲንን በመጥቀስ ነው። አክለውም ስብ እንዲሁም ሚነራል የተሰኙትንም ንጥረ ምግቦች ከሥጋ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
ዶ/ር ካሌብ ባዬ በበኩላቸው ጥሬ ሥጋ ውስጥ አይረን እና ዚንክ የመሳሰሉ ማዕድናት እንደሚገኙ ይናገራሉ።
የሥነ ምግብ ተመራማሪው ዶ/ር ይሁኔ በበኩላቸው ከብቶች እጽዋትን ተመግበው ያከማቿቸውን ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ዶ/ር ይሁኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት የጥሬ ሥጋ መመገብ ባህል መኖሩን በመጥቀስ፣ ተመጋቢዎችን ጥሬ ሥጋ አትመገቡ ብሎ ከመምከር ይልቅ የእንስሳው ጤንነት የተመረመረ እና የሥጋው ምንጭ በደንብ የታወቀ መሆን እንደሚገባው ይመክራሉ።
የሥነ ምግብ ተመራማሪዎቹ ጥሬ ሥጋ መመገብ ለጤና ያለውን አሉታዊ ጎን ሲያስረዱ ከእንስሳው ጤንነት ይጀምራሉ።
እንስሳው በተለያዩ በሽታዎች የተጠቃ ከሆነ እና ተገቢውን የህክምና ክትትል ያላደረገ ከሆነ፣ በአስተራረዱ ወቅትም ጥንቃቄ ካልተደረገ ከዚያም በኋላ ቢሆን ሥጋው በሚቀመጥበት ወቅት በአግባቡ ካልተያዘ ተመጋቢው ላይ የጤና እክል ማስከተሉ አንደማይቀር ይጠቅሳሉ።
የኮሶ ትል፣ ሳልሞኔላ እና አንትራክስ የተሰኙ በሽታዎች ከጥሬ ሥጋ ጋር ተያይዞ ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል።
የእንስሳት ህክምና ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ደመቀ ወንድምአገኝ እንደሚሉት በሬውን ከማደለብ ጀምሮ ለምግብ እስከሚቀርብ ድረስ ባለው ጊዜ ያለው ንጽህና ካልተጠበቀ ለእነዚህ ህመሞች ሊያጋልጥ ይችላል።
በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የሥነ ምግብ ተመራማሪዎቹ ዶ/ር ይሁኔ እና ዶ/ር ካሌብ በበኩላቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።
ሥጋው በስሎ ለምግብነት ዝግጁ በሚሆንበት ወቅት ግን እነዚህ በሽታ አምጭ ተህዋሲያን ሊጠፉ እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
ሌላው የበሰለ ምግብን መመገብ በሰውነታችን በቀላሉ እንዲፈጭ እና ልሞ በውስጣችን እንዲዋሀድ ያደርገዋል።
የሥነ ምግብ ተመራማሪዎቹ ከጤናም ሆነ ከደኅንነት አንጻር ሥጋ በስሎ ቢበላ የተሻለ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ቢቢሲ ለተመራማሪዎቹ ያቀረበው ሌላው ጥያቄ ከጥሬ ሥጋ አንጻር ከበሬ፣ ከበግ እና ከፍየል የትኛው ይመረጣል የሚል ነው።
ለዲላ ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ይሁኔ፣ በሦስቱም እንስሳት ሥጋ ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ምግቦች ተመሳሳይ ናቸው።
አክለው ግን ጥሬ ሥጋ የሚመገቡ ሰዎች ውፍረትን ለመቀነስ እንዲረዳቸው ከጮማ ነጻ የሆነውን ቢመገቡ ሲሉ ይመክራሉ።
ጮማ የሚመገቡ ሰዎች ሰውነት ከሚፈልገው በላይ ስብ ከመመገብ በመቆጠብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ይመክራሉ።
በተለይ ዓውድ ዓመትን ተከትሎ የሚበላ የጮማ መጠን “ከልክ ያለፈ እና በሽታ ላይ የሚጥል” የአመጋገብ ሥርዓት መሆኑን የታዘቡት ምሁሩ፣ ይህ መገራት እንዳለበት ይናገራሉ።
በሰውነታችን ውስጥ ጮማ የሚሰራቸው ብዙ ሕይወታዊ ክንውኖች አሉ የሚሉት ዶ/ር ይሁኔ፣ ነገር ግን መጠኑን መወሰን ተገቢ ነው ሲሉ ይመክራሉ።
ከመጠኑ ያለፈ ቀይ ሥጋን መመገብ ለልብ፣ ለስትሮክ እና ለካንሰር በሽታዎች እንደሚያጋልጥም ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
ጥሬ ሥጋ እና ዓውድ ዓመት
ዓውድ ዓመትን ዓውድ ዓመት ከሚያሰኙ ነገሮች መካከል ሁሉም እንደአቅሙ የሚዘጋጃቸው የበዓል ምግቦች እና መጠጦች ከፍ ያለ ድርሻ አላቸው።
የወዳጅ ዘመድ መጠያየቅ፣ የቡናው መጫጫስ፣ የቄጠማው መጎዝጎዝ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት በምግብ እና በመጠጡ ላይ የሚጨመሩ ሰበዞች ናቸው።
በተለይ እንደ ገና እና ፋሲካ ያሉ ትላልቆቹ ዓውደ ዓመቶች የሚመጡት ረዥም የጾም ወቅትን ተከትለው በመሆናቸው አቅም በፈቀደ ሁሉ እርድ ይከናወናል።
ከዚያ በኋላ ዳቢት ከሻኛ መቁረጥ፣ ጥብስ ከክትፎ እያመራረጡ ማወራረድ፣ ቀዩን ካልጫው እያጣቀሱ መጉረስ የዓውድ ዓመት ቱርፋቶች ናቸው።
በዚህ ሁሉ ደግሞ አውራውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ ጥሬ ሥጋ መመገብ ነው።
ጥሬ ሥጋ የሚመገቡ ሰዎች ማኅበራዊ ትስስራቸውን እግረ መንገድ ያጠናክራሉ።
በዓውድ ዓመት ሰብሰብ ብለው ልኳንዳ ቤት በመሄድ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ገቢ አቅማቸው በጋራ በመሆን ቅርጫ በመግባት አንድ በሬን በቡድን በመካፈል አብሮነታቸውን ያጠናክራሉ።
ጥሬ ሥጋ አፍቃሪያን የበሬው ከየት መጥነት ይጠይቃሉ።
በተለይ የሐረር እና የጅሩ ሰንጋዎችን ለጥሬ ሥጋ ይመርጧቸዋል።
አሁን አሁን ደግሞ የደለበ በሬ ለሥጋው ተመራጭ ሲሆን ይስተዋላል።
ከዚህ ሁሉ ባሻገር የጥሬ ሥጋ ግርማ ሞገስ የሚደምቀው ከማባያው ጋር ሲሆን ነው።
አዋዜ፣ ሰናፍጭ፣ ዳጣ እና ሚጥሚጣ ጥሬ ሥጋን መልከ ብዙ ለማድረግ ያጅቡታል።
ማወራረጃ ጠላ፣ ጠጅ፣ አረቄ፣ ወይን አልያም ቢራም አብረው የሚቀረቡ መጠጦች ናቸው።
ከደለበ ይልቅ ያረሰ በሬ
ለዶክተር ይሁኔ የእንስሳቱን ሥጋ ለመምረጥ በዋናነት አመጋገባቸው ምክንያት እንደሚሆን ያስረዳሉ።
ለምሁሩ ከሚደልቡ ከብቶችይልቅ ግጦሽ ላይ ተሰማርተው ያደጉ እንስሳትን በሥጋቸው ይዘት ይመርጧቸዋል።
ከአመንዣጊ እንስሳት ሥጋ ይልቅ ደግሞ የዶሮ እና የዓሳ ሥጋን ለምግብነት መምረጥ ያለው የጤና ጥቅም የተሻለ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ለሥጋ ምርታቸው የሚመረጡ እንስሳት ላይ ዋነኛው ጥያቄ መሆን ያለበት፣ እንስሳቱ እንዴት እና የት ነው ያደጉት የሚለውን ነው ይላሉ የሥነ ምግብ ባለሙያው።
ከደለቡ ከብቶች ይልቅ ያረሱ ከብቶች ሥጋ ከጤናማነት ረገድ ተመራጭ መሆኑንም አክለው ያብራራሉ።
እንዳይንቀሳቀሱ ሆነው በሆርሞን ከደለቡ ከብቶች ይልቅ በተፈጥሮ ግጦሽ ያደጉ እንስሳት የበለጠ ሥጋቸው ተፈላጊ ነው።
የሥጋ ደረጃ ሲወጣ በቀዳሚነት ታድኖ የሚገኝ ሥጋ፣ በመቀጠል ካረሱ ከብቶች የሚገኝ፣ ከዚያም ከጋጡ ከብቶች በመቀጠልም ከደለቡ ከብቶች የሚገኝ ሥጋ በቅደም ተከተል እንደሚመቀመጥ ምሁሩ ያስረዳሉ።
ይህም የሆነው ከሥጋ የሚገኘው ስብ ውስጥ ያለው የኦሜጋ 3 እና 6 መጠን በደለቡ ከብቶች ውስጥ ካረሱ ከብቶች በተለየ በዝቶ መገኘቱ ለጤና ያለው ጠቀሜታ ላይ ጥያቄ ስለሚያስነሳ ነው።
ስለዚህ የእንስሳት ሥጋን ለመምረጥ በዋናነት መስፈርት መሆን ያለበት አመጋገባቸው ነው።
ዶ/ር ካሌብ ባዬ በበኩላቸው የጥሬ ሥጋ አመጋገብን በረመለከተ አንድ ተጨማሪ ጠቃሚ ነጥብ ማንሳት ይፈልጋሉ።
ጥሬ ሥጋ መመገብ ቶሎ የመጥገብ ስሜትን ስለማያመጣ ከተገቢው መጠን በላይ መውሰድ ሊኖር ይችላል። ስለዚህም በጥሬ ሥጋ አመጋገባችን ወቅት ጤናን፣ ማኅበረሰብን፣ ቤተሰብን እና ኢኮኖሚን ከግንዛቤ ማስገባት ተገቢ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ለዚህም ከንጥረ ነገር ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሁኔታም አንጻር ጥሬ ሥጋ መመገብ የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው ዶ/ር ካሌብ ያስረዳሉ።
አንድ ኪሎ ጥሬ ሥጋን በውድ ዋጋ ገዝቶ ከመመገብ ይልቅ ወደ ቤት ወስዶ ተካፍሎ መብላት ማኅበረሰባዊ እና ቤተሰባዊ ሁኔታ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ይጠቅሳሉ። (BBC)