የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጠቃላይ በስራ ላይ ያሉ አውሮፕላኖች አሁናዊ ዋጋ 5 ነጥብ 25 ቢሊየን ዶላር መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህም በአፍሪካ ካሉት የአውሮፕላኖች ዋጋ 32 በመቶውን የሚሸፍን ነው ተብሏል።
እንደ ch-aviation.com ዘገባ በኢትዮጵያ 119 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ 89 ጠባብ እና ሰፊ አውሮፕላኖች እንዲሁም 30ዎቹ ደግሞ በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ በረራ የሚውሉ መለስተኛ አውሮፕላኖች ናቸው።
14 ቦይንግ 737 ማክስ፣ 18 787 ድሪምላይነርስ እና 20 ኤርባስ ኤ350-900 ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን አውሮፕላኖች የአየር መንገዱ ንብረቶች መሆናቸውን ዘገባው ያመላክታል።
ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ በአፍሪካ በአውሮፕላኖች አሁናዊ ዋጋ ከኢትዮጵያ ጋር ቀዳሚዎቹ አምስት ሀገራት ሆነዋል።
የኢትዮጵያ የአውሮፕላኖች የገበያ ዋጋ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ካለችው ግብፅ በ50 በመቶ የሚጠጋ ብልጫ አለው፡፡
የአፍሪካ አየር መንገዶች በሚቀጥሉት 5 አመታት አዳዲስ እና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን አውሮፕላኖች መረከብ የሚጀምሩ ሲሆን ኢትዮጵያም ቀዳሚውን ስፍራ እንደምትይዝ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈረንጆች 2035 ያለውን የበረራ ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ ከዓለም ምርጥ አየር መንገዶች ጋር ለመወዳደር አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።
ፋና